ትራምፕ ፍሊጤማውያንን ከጋዛ ለማፈናቀል የያዙት እቅድ “መቼም የማይሳካና ትልቅ ወንጀል ነው”- አል ሻራ
የሶሪያ ፕሬዝዳንት አል ሻራ “የትኛወም ኃይል ፍሊስጤማውያንን ከመሬታቸው ማፈናቅል አይችልም” ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/252-211350-whatsapp-image-2025-02-11-at-8.12.51-pm_700x400.jpeg)
ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር በያዙትን እቅዳቸው ቢጸኑም በርካታ ሀገራት በመቃወም ላይ ይገኛሉ
የሶሪያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍሊጤማውያንን ከጋዛ ለማፈናቀል የያዙት እቅድ መቼም የማይሳካ ነው አሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ኃውስ እንደገቡ የጋዛ ፍርስራሽ እስኪጸዳ ድረስ ፍልስጤማውያን እንደ ግብጽ እና ዮርዳኖስ ባሉ ሀገራት እንዲጠለሉ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማፈናቀል በያዙት እቅድ ላይ መጽናታቸውን በድጋሚ ያረጋገጡ “ፍልስጤማውያን ከጋዛ በቋሚነት ይወገዳሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
የሶሪያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ የትራምፕን ንግግር በተቃወሙበት መግለጫቸው፤ “ትራምፕ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ በማፈናቀል ወደመ ሌላ ስፍራ ለማዛወር እና ግዛቱን ለመቆጣጠር ያቀዱት እቅድ "ትልቅ ወንጀል እና የማይሳካ ነው” ብለዋል።
አል ሻራ አክለውም፤ “የአንድ ሀገር ህዝብ መሬታቸውን ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድድ ምንም አይነት ሃይል የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ህዝቡ ስቃይ፣ ግድያና ውድመት ታግሶ መሬቱን ሳይለቅ እስካሁን ቆይቷል ያሉት አል ሻራ፤ ባለፉት 80 ዓመታት ውስጥ ሰዎችን ከሀገራቸው ለማፈናቀል የተደረገው ሙከራ ሁሉ አልተሳካም፤ የፍልስጤም ትውልዶች የሚያውቁት አንድ ትምህርት አለ, እሱም በመሬታቸው ላይ መጣበቃቸውን ነው ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ በርካታ የዓለም ሀገራት በመቃወም ላይ ይገኛሉ።
የጋዛ ተፈናቃዮችን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት እንዲያስጠልሉ ከትራምፕ ትእዛዝ የተሰጣቸው ግብጽ እና ዮርዳኖስ እቅዱን ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፥ የፍልስጤም እና የአረብ መሪዎችም አጥብቀው ተቃውመውታል።
በትራምፕ ውሳኔ የተገረሙ እና የተደናገጡ የጋዛ ነዋሪ ፍሊጤየማውያንም “ጋዛን ለቀን አንወጣም” ሲሉ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።
“ነፍሳችንን ቢያስከፍለን እንኳን ጋዛን አንለቅም” ያሉት የጋዛ ነዋሪ ፍሊስጤማውያን፤ “የትራምፕን ውሳኔ እንቃወማለን፣ ጦርቱን አስቁሟል፤ ነገር ግን እኛን ማፈናቀል ህይወታችን እንዲያበቃለት ያደርጋል” ብለዋል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምት መደረሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍሊስጤማውያን ወደ ፈራረሰቸው መንደራቸው እየተመሙ ይገኛሉ።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ከሆነ ከአጠቃላይ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል 1.9 ሚሊየን ወይም 90 በመቶው በ15 ወሩ ጦርት ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።