ሰሜን ኮሪያ "በአሜሪካ ተንኳሽነት" ምክንያት የህገ-መንግስት ማሻሻያ አደረገች
ፒዮንግያንግ 'የመኖር ዋስትናን ለመጠበቅና ጦርነትን ለመከላከል' እርምጃውን መውሰዷን ተናግራለች
የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ኃይል ግንባታ ፖሊሲ መሰረታዊ ህግ ተደርጓል
ሰሜን ኮሪያ "በአሜሪካ ተንኳሽነት" ምክንያት የህገ-መንግስት ማሻሻያ አደረገች።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ልማቷን ለመጠበቅ የህገ-መንግስት ማሻሻያ ማድረጓን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኸን ዘግበዋል።
የሀገሪቱ መሪዎች "የአሜሪካን ተንኳሽነት" ለመከላከል የኒውክሌር መሳሪያዎችን በፍጥነት ለማምረት ቃል ገብተዋል።
ህግ የማውጣት ስልጣን ያለው የሀገሪቱ ከፍተኛ ህዝባዊ ጉባኤ "የፒዮንግያንግን የመኖር ዋስትና ለመጠበቅና ጦርነትን ለመከላከል" ሲል ማሻሻያውን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል ተብሏል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በጉባኤው ተገኝተው "የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ኃይል ግንባታ ፖሊሲ መሰረታዊ ህግ ሆኖ ቋሚ እንዲሆን ተደርጓል። ማንም ሰው በምንም ነገር እንዲሽረው አይፈቀድም" ብለዋል።
ኪም አክለውም "የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እና የኒውክሌር ጥቃትን ለማስፋፋት እንዲሁም በተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ለማሰማራት በሚደረገው ጥረት ወደፊት መግፋት አስፈላጊ ነው" ሲሉ አሳስበዋል።
የአሜሪካ የጦር ልምምዶችና በቀጣናው የሚደረግ ስልታዊ አጋርነት ከፍተኛ ትንኮሳ ነው ብለዋል።
የፒዮንግያንግ ጎረቤቶች ደቡብ ኮሪያና ጃፓን የህገ-መንግስት ማሻሻያውን የደህንነት ስጋት ነው ያሉ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህን መታገስ የለበትም ሲሉ አቋማቸውን ተናግረዋል።