ደቡብ ኮሪያ ከ10 አመት በኋላ ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት አቀረበች
ከ6 ሺህ 700 በላይ ወታደሮች የተሳተፉበት ወታደራዊ ትርኢት ለፒዮንግያንግ ግልጽ መልዕክት ማስተላለፊያ ነው ተብሏል
በትርኢቱ ደቡብ ኮሪያ በራሷ አቅም የሰራችውን የውጊያ ጄት እና አዳዲስ ድሮኖች ለእይታ አቅርባለች
ደቡብ ኮሪያ ከ10 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት አቅርባለች።
ሰሜን ኮሪያ በየአመቱ ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት ስታሳይ ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ግን በየአምስት አመቱ የማሳየት ልምድ ነበራት።
ሴኡል ከወታደራዊ ክብረበዓል ጋር አስታካ የምታቀርበውን ወታደራዊ ትርኢት ለመጨረሻ ጊዜ ያካሄደችው በ2013 ነበር።
ከአምስት አመት በኋላ (በ2018) ግን ከፒዮንግያንግ ጋር ግንኙነታቸውን ማለዘብ ይፈልጉ የነበሩት የወቅቱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሙን ጃይ ኢን ወታደራዊ ትርኢቱ እንዳይቀርብ አድርገዋል።
ባለፈው አመት ወደ ስልጣን የመጡትና ከሰሜን ኮሪያ ጋር አይን እና ናጫ የሆኑት ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በበኩላቸው ከ2013 በኋላ ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት እንዲቀርብ አድርገዋል።
የዛሬው ወታደራዊ ትርኢት ከ6 ሺህ 700 በላይ የደቡብ ኮሪያ እና 300 የአሜሪካ ወታደሮች የተሳተፉበት ነው።
ከ340 በላይ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ለእይታ የቀረቡበት ትርኢት፥ ደቡብ ኮሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በራሷ አቅም የሰራችው “ኬኤፍ - 21” የውጊያ ጄት እና አዳዲስ ድሮኖች እንዲሁም ሚሳኤሎች ያሳየችበት ነው ብሏል አሶኤትድ ፕረስ በዘገባው።
የደቡብ ኮሪያ ጦር 75ኛ አመት የምስረታ በዓል በሴኡል ሲከበር ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የአሜሪካና የሀገራቸውን ወታደራዊ ትብብር እየተጠናከረ መሄድ አድንቀዋል።
“ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን ከተጠቀመች የሀገሪቱ ስርአት በአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ከባድ ምላሽ ፍጻሜውን ያገኛል” ነው ያሉት።
በጦር መሳሪያ ሽያጭ ከቀዳሚዎቹ ሀገራት የምትጠቀሰው ደቡብ ኮሪያ እንደ ዩክሬን ላሉ በጦርነት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት መሳሪያዎቿን መሸጥ የሚከለክል ፖሊሲ አላት።
ይሁን እንጂ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ መሳሪያዎቿን ካቀረበች ሴኡልም ለኬቭ ለመሸጥ ልትስማማ እንደምትችል ተንታኞች ያነሳሉ።
ደቡብ ኮሪያ ባለፈው አመት ብቻ ለፖላንድ 12 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ታንኮች እና መድፎችን መሸጧን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አስታውሷል።
በዛሬው እለት ለእይታ ያቀረበቻቸው አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችም ለጎረቤቷ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ከማስተላለፍ ባሻገር በጦር መሳሪያዎች ልማት የደረሰችበትን ደረጃ ለአለም ያሳየችበት ነው ተብሏል።