ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያውን መሪ “የአሜሪካ ድምጽ ማጉያ አሻንጉሊት” ነው በሚል ወረፈች
ፒዮንግያንግ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በተመድ 78ኛ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ቅር መሰኘቷን በስድብ በተሞላ መግለጫ ገልጻለች
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የጎረቤቷን መግለጫ “ፕሮቶኮል ያልጠበቀ እና ክብረነክ” ነው ብላዋለች
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ያስተላለፉት መልዕክት ጎረቤት ሰሜን ኮሪያን አስቆጥቷል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ መፈቀድ የለበትም ማለታቸው ይታወሳል።
ፒዮንግያንግ እና ሞስኮ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ላይ ከደረሱ ሴኡል እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥም በንግግራቸው አንስተዋል።
የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ሀገራት ከጎረቤቶቻቸውም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የማጠናከር “ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብታቸው ነው” ብሏል።
መግለጫው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልን “አሻንጉሊት”፣ “የአሜሪካ ድምጽ ማጉያ”፣ “የቆሸሸ ጭንቅላት” ያለው እና “ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ያልዘለቀው” በሚሉ ቃላት ወርፏል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ደቡብ ኮሪያ በሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ግንኙነት ዙሪያ አስተያየት የመስጠት መብት እንደሌላትም ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጿል።
ባለፈው አመት ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነታቸውን ያጠበቁት ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በፒዮንግያንግ የስድብ ናዳ የወረደባቸው የመጀመሪያው መሪ አይደሉም።
የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንቶችን ሊዩንግ ባክ እና ፓርክ ጊዩን ሃይን አይጥ” እና “ሴተኛ አዳሪ” ፤ ዶናልድ ትራምፕ እና ባራክ ኦባማን ደግሞ “የአዕምሮ ውስንነት ያለበት ድንክ” እና “ዝንጀሮ” በሚል ጸያፍ ቃላት መሳደቧ ይታወሳል።
የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮ ዮንግሳም፥ የሰሜን ኮሪያ የቴለኢቪዥን ጣቢያ ፕሬዝዳንት የልን የገለጸበት መንገድ የሀገሪቱ መንግስት ምን ያህል ከፕሮቶኮልና ዲሲፕሊን እንደራቀ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተያያዘ ዜና የደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ባህር ሃይሎች ለሶስት ቀናት የሚዘልቅ የጋር ልምምዳቸውን በዛሬው እለት በምስራቃዊ የኮሪያ ልሳነ ምድር መጀመራቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።