ደቡብ ኮሪያ፤ ዜጎቿ የሰሜን ኮሪያ ሚዲያዎች እንዲከተታሉ እንደምትፈቅድም አስታውቃለች
ደቡብ ኮሪያ “ሁለቱን ኮሪያዎቸ ማዋሃድ” የ2023 እቅዷ መሆኑን ገለጸች።
የሀገሪቱ የውህደት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ደቡብ ኮሪያ በያዝነው ዓመት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጋር ያላትን ግንኙነት "መደበኛ" ለማድረግ ትሰራለች ብሏል።
ሚኒስቴሩ የ2023 ዋና ዋና ተግባራትቱን በተመለከተ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ባቀረበው ሪፖርት ሰባት ዋና ዋና የፖሊሲ ግቦችን በዝርዝር አስቀምጧል።
- ደቡብ ኮሪያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት የተለያዩ ቤተሰቦች እንዲገናኙ ከሰሜን ኮሪያ ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ገለጸች
- ከሰሜን ኮሪያ መሪ ለቀድሞ ደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የተሰጡ ውሾች በበጀት እጥረት ምክንያት ወደ መካነ እንስሳት ተወሰዱ
ይህም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለው የቀዘቀዘ ግንኙነትን በማሻሻል እና በቀጣይ ሁለቱም ኮሪያዎች የሚዋሃዱበት መንገድን ለማመቻቸት ያለመ መሆኑን የደቡብ ኮሪያ የዜና ወኪል ዮንሃፕ ዘግቧል።
ሚኒስቴሩ “የሻከረውን የኮሪያን ግንኙነት ለማሻሻል ዕድሎችን ለመፈለግ በሲቪክ ቡድኖች እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት ከሰሜን ኮሪያ ጋር በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ለማድረግ ማቀዱን” ገልጿል።
በሁለቱም ኮሪያዎች መካከል ያለው ውይይት ከቀጠለ እንደፈረንጆቹ ከ1950 እስከ 1953 በተካሄደው ጦርነት የተለያዩ ቤተሰቦች እና በሰሜን ኮሪያ ታስረው የሚገኙትን ደቡብ ኮሪያውያን ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ይሆናልም ብሏል ሚኒስቴሩ ።
“ኒው ፊውቸር ኢኒሼቲቭ ኦን ዩኒፊኬሽን” የተሰኘ ውህደቱን በመካከለኛ እና ረጅም እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል እቅድ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑም ጭምር አስታውቋል።
በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለውን "ብሄራዊ ስምምነት" ወደነበረበት ለመመለስ በሰሜን ኮሪያ ሬዲዮ፣ ሚዲያ እና ህትመቶች ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚነሳ የኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ቀደም ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።
በዚህም ለሰሜን ኮሪያ የሬድዮ ስርጭቶች እና ሚዲያዎች በር የመክፈት ጉዳይን በተመለከተ፤ ሚኒስቴሩ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ዜጎች የሰሜን ኮሪያ ዋና ጋዜጣ የሆነውን ‘ሮዶንግ ሺንሙን’ እንዲያነቡ እንደሚፈቅድ አስታውቋል።
ደቡብ ኮሪያ ይህን ትበል እንጅ በሰሜን ኮሪያ በኩል እስካን የተባለ ነገር የለም።
ደቡብ ኮሪያ ይህን ትበል እንጅ ሰሜን ኮሪያ በተለያዩ ጊዜያት በምታካሂዳቸው የሚሳኤል ሙከራዎች በኮሪያ ልሳነ ምድር አሁንም ውጥረት እንደነገሰ ነው።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሶክ ዮል ፒዮንጊያንግ የኒውክሌር ማበልጸግ መርሃ-ግብር ካቆመች ሴኡል ለሰሜን ኮሪያ የኢኮኖሚ መሻሻል ድጋፍ ታደረግላቸው በሚል ባለፈው ዓመት ያሳዩት"ድፍረት የተሞላበት ተነሳሽነት" ሰሜን ኮሪያ ውድቅ ማድረጓ የሚታወስ ነው።