የሁለቱን ኮሪያዎች ውህደት የሚያመለክተው ሀውልት መፍረሱ ተገለጸ
ሰሜን ኮሪያም በደቡብ ኮሪያ እና በአሜሪካ ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ ደቡብ ኮሪያን አጠፋለሁ ስትል ዝታለች
ኪም የሀገሪቱ ህገመንግስትም ደቡብ ኮሪያ "ቀዳሚ ጠላት" የሚል አንቀጽ እንዲካተትበት ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል
ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚኖራትን ውህደት የሚያሳየውን ሀውልት ማፍረሷ ተገለጸ።
ባለፈው ሳምንት ደቡብ ኮሪያ "ቁጥር አንድ ጠላት" ነች ባሉት እና ውህደት እንደማይሳካ በገለጹት ኪም ጆንግ ኡን ትዕዛዝ፣ ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚኖራትን የመልሶ ውህደት የሚያመለክተው ሀውልት ፈርሷል።
በ2000 ከተካሄደው ታሪካዊ የኢንተር ኮሪያ ጉባኤ በኋላ የቆመው የሁለቱን ኮሪያዎች የመዋሀድ ተስፋ የሚያመለክተው ሀውልት አሁን ላይ አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮይተርስ በዘገባው የመልሶ ውህደትን የሚሳየው ምልክት መውደሙን ማረጋገጥ እንደማይችል ጠቅሷል።
ባለፈው ጥር 15፣2024 በተካሄደው ጉባኤ ላይ ሀውልቱን "አስቀያሚ" ያሉት ኪም የሀገሪቱ ህገመንግስትም ደቡብ ኮሪያ "ቀዳሚ ጠላት" የሚል አንቀጽ እንዲካተትበት ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሰሜን ኮሪያ ከጠላቶቿ ጋር የኑክሌር ጦርነት ለማድረግ ዝግጁነቷን መግለጿን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ በሚያደርጉት ወታደራዊ ልምምድ ምክንያት በኮሪያ ባህረሰላጤ ውጥረት ነግሷል።
"ዘ ስሪ ቻርተር ኦፍ ሪዩኒፊኬሽን" የተሰኘው ሀውልት 30 ሜትር ርዝመት እንዳለው ተገልጿል።
የደቡብ ኮሪያ መንግስት መዛግብቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ "ሶሪ ቻርተር" ራስን መቻልን፣ ሰላምን እና ብሔራዊ ትብብርን የሚያመለክት ነው።
በ2022 ስልጣን የተረከቡት የደቡብ ኮሪያው ዩን ሱክ የኦል ሰሜን ኮሪያ ለምትወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ጠንካራ ምላሽ ይሰጣል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ሰሜን ኮሪያም በደቡብ ኮሪያ እና በአሜሪካ ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ ደቡብ ኮሪያን አጠፋለሁ ስትል ዝታለች።
ሰሜን ኮሪያ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ በ2018 ወታደራዊ ውጥረትን ለማርገብ ለተደረሰው ስምምነት እንደማትገዛ ማሳወቋም ይታወሳል።