ፑቲን ፒዮንግያንግን በቅርቡ እንደሚጎበኙ ሰሜን ኮሪያ ገለጸች
ጉብኝቱ የሩሲያ መሪ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ሰሜን ኮሪያን ሲጎበኝ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሏል
ፕሬዝደንት ፑቲን ፈቃደኝነታቸውን የገለጹት ባለፈው ሳምንት ከሰሜን ኮሪያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በሩሲያ በተገናኙበት ወቅት ነው
ፕሬዝደንት ፑቲን ፒዮንግያንግን በቅርቡ እንደሚጎበኙ ሰሜን ኮሪያ ገለጸች።
ፑቲን ባለፈው ሳምንት ከሰሜን ኮሪያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ሶን ሁዋይ ጋር በሩሲያ በተገናኙበት ወቅት ፒዮንግያንግን ለመጎበኘት ያላቸውን ፈቃደኝነት መግለጻቸውን ሮይተርስ የሰሜን ኮሪያውን ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
ፑቲንም ለተደረገላቸው ግብዣ ምስጋና ማቅረባቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ጉብኝቱ የሩሲያ መሪ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ሰሜን ኮሪያን ሲጎበኝ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሏል።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በሰሜን ኮሪያ ግብዣ የሚደረገው የፑቲን ጉብኝት በቅርቡ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ነገርግን ቃል አቀባዩ ጉብኝቱ መቼ ይሁን የሚለው ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን አልገለጹም።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ሶን ሁዋይ ጉብኝት ወቅት ሩሲያ ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን በምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ላሳየችው ድጋፍ እና አጋርነት አመስግናለች።
በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ አብረው ለመስራት የተስማሙት ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ፣ የአሜሪካ ትንኮሳ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸው የተመድ መተዳዳሪ ደንብን መሰረት ያደረገ መሆኑን በመግለጽ የሚነሳባቸውን ትችት ይከላከላሉ።
በፈረንጆቹ 1999 ከቦሪስ የልስቲን ስልጣን የተረከቡት ፑቲን በ2000 ፒዮንግያንግን በመጎብኘት ከኪም ጆንግ ኡን አባት ኪም ጆንግ ሁለተኛ ጋር ተገናኝተው ነበር።
የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያን ግንኙነት መጠናከር አሜሪካን እያሳሰባት ነው።
ፑቲን የኪምን የጉብኝት ግብዣ የተቀበሉት ባለፈው መስከረም ወር በሩሲያ በተገናኙበት ወቅት ነበር።