ሰሜን ኮሪያ በ2024 የመጀመሪያዋን ባለ'ሶሊድ ፊውል' ሚሳይል አስወነጨፈች
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አዛዥ ሚሳይሉ በኮሪያ ባህረሰላጤ እና በጃፖን መካከል በሚገኘው ውሃማ አካል ከማረፉ በፊት በሰአት 1000 ኪሎሜትር ይምዘገዘግ ነበር ብለዋል
ሰሜን ኮሪያ ሩቅ የሆኑ የአሜሪካ ኢላማዎችን ለመምታት በቀላሉ የማይታዩ ወይም ዲቴክት የማይደረጉ መሳሪያዎችን ለመስራት እየጣረች ነው ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ በ2024 የመጀመሪያዋ የሆነውን 'ሶሊድ ፊውል' የሚጠቀም ሚሳይል አስወነጨፈች።
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት እንዳስታወቀችው በፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያዋ የሆነውን አዲስ 'ሶሊድ ፊውል' ወይም ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀም የመካከለኛ እርቀት ሚሳይል አስወንጭፋለች።
ሮይተርስ እንደዘገው ከሆነ ሀገሪቱ ያስወጨፈችው ሚሳይሉ ሃይፐርሶኒክ ዋርሄድ ወይም ፈንጅዎች ያለው ነው።
ሰሜን ኮሪያ ሩቅ የሆኑ የአሜሪካ ኢላማዎችን ለመምታት በቀላሉ የማይታዩ ወይም ዲቴክት የማይደረጉ መሳሪያዎችን ለመስራት እየጣረች ነው ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማስወንጨፏን ይፋ ያደረገችው፣ የደቡብ ኮሪያ እና የጃፖን ወታደራዊ ባለስልጣናት ከሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ በቅርብ እርቀት ከሚገኝ ቦታ የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ መደረጉን ከደረሱበት ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ይህ ሙከራ የተደረገው ሰሜን ኮሪያ ላበለጸገችው የባለሶሊድ ፊውል የመካከለኛ እርቀት ሚሳይል የሚሆነውን ሞተር ወይም ኢንጂን በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን ከገለጸች ከሁለት ወራት በኋላ መሆኑም ተገልጿል።
ኮሪያን ሴንትራል ኒውስ የተባለው የሰሜን ኮሪያ የመንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ከሆነ ሙከራው የተደረገው የሶሊድ ፊውል ኢንጂን የሚጠቀም ሚሳይል ያለውን አስተማማኝነት እና የሀይፐርሶኒክ ዋርሄድን ፍጥነት ለማረጋገጥ የተደረገ ነው።
ሙከራው ስኬታማ መሆኑን የገለጸው ጣቢያው የበረራ ዝርዝሩን ግን ይፋ አላደረገም።
የሀገሪቱን የጦር መሳሪያ ልማት በዋናነት የሚመሩት መሪው ኪም ጆንግ ኡን በሙከራው ወቅት መገኘታቸው ወይም አለመገኘቻቸው አልታወቀም።
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አዛዥ እንደተናገሩት ሚሳይሉ በኮሪያ ባህረሰላጤ እና በጃፖን መካከል በሚገኘው ውሃማ አካል ከማረፉ በፊት በሰአት 1000 ኪሎሜትር ይምዘገዘግ ነበር ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ በጉዋም የሚገኘውን የአሜሪካ የጦር ሰፈር ሊመታ ይችላል የተባለውን ህዋሶንግ-12 ጨምሮ ያሏት የመካከለኛ እርቀት ሚሳይሎች ፈሳሽ ነዳጅ የሚጠቀሙ ናቸው።
ፈሳሽ-ነዳጅ የሚጠቀሙ ሚሳይሎች ከመወንጨፋቸው በፊት ነዳጅ መሞላት ያለባቸው እና ለረጅም ጊዜ ነዳጅ ተሞልተው መቆየት የማይችሉ ሲሆኑ ሶሊድ ፊውል የሚጠቀሙት በፍጥነት ለማስወንጨፍ ይመቻሉ።
ደቡብ ኮሪያን እና አጋሯን አሜሪካን በስጋት የምታየው፣ ሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማልማቷን እና መሞከሯን ቀጥላበታለች።