ሰሜን ኮሪያ መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አስወነጨፈች
ደቡቡ ኮሪያ እና ጃፓን ከአሜሪካ ጋር በመተባበር አዲሱን የሚሳኤል ሙከራ እየመረመርን ነው ብለዋል
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሩሲያ የሶስት ቀናት ጉብኝት ያደርጋሉ
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት መካከለኛ ርቀት (ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ 500 ኪሎሜትር) ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አስወነጨፈች።
ባለስቲክ ሳይሆን አይቀሮም የተባለው ሚሳኣል በጃፓን የኢኮኖሚ ዞን መውደቁን የጃፓን የባህር ዘብ አስታውቋል።
ደቡብ ኮሪያም ከፒዮንያንግ አቅራቢያ በተተኮሰው ዙሪያ ከጃፓን እና አሜሪካ ጋር ምርመራ እያደረገች መሆኑን ነው የገለፀችው።
በቅርቡ የስለላ ሳተላይት ያመጠቀችውና ሀይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል የሞከረችው ፒዮንግያንግ ከጎረቤቶቿና ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫዋ እየናረ ነው።
ሴኡልን "ዋነኛ ጠላት" አድርጋ የፈረጀችው ሰሜን ኮሪያ የውህደት ውጥኑ እንደማይሰምር መግለጿ ይታወሳል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጦራቸው በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅና የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ምርት እንዲበራከት ባዘዙ ማግስት ፒዬንግያን ሁለቱን ኮሪያዎች በሚለየው ድንበር ከባድ መሳሪያዎቿን አስጠግታለች ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በታህሳስ ወር አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል የሞከረችው ሰሜን ኮሪያ ከሞስኮ ጋር ትብብሯን እያጠናከረች ነው።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ሶን ሁይ ከነገ ጀምሮ የሶስት ቀናት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ሞሶኮ በዩክሬኑ ጦርነት የሰሜን ኮሪያን ሚሳኤሎች ተተጠቅሜማለች የሚሉ ሪፓርቶች በቅርቡ መውጣታቸው አይዘነጋም።
ሩሲያም ሆነች ሰሜን ኮሪያ የመሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ላይ እንዳልደረሱ ቢገልፁም ባለፈው አመት ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማምተዋል።
የሴኡልና ዋሽንግተን ትብብር በአንድ ወገን የፒዮንግያንግና ሞስኮ በሌላ የኮሪያን ልሳነ ምድር ውጥረት በየእለቱ እንዲንር እያደረገው ነው።