ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ልታጠናክር እንደምትችል ገለጸች
ፕሬዝዳንት ፑቲን የነጻነት ቀን በዓሏን አስመልክተው ለመሪው ኪም ጆንግ ኡን ደብዳቤ ጽፈዋል
የኮሪያ ልሳነ ምድር ከጃፓን አገዛዝ ነጻ የወጣችበት ቀን በዓል ዛሬ ለ77ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሃገራቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ልታጠናክር እንደምትችል ገለጹ።
ፑቲን የሰሜን ኮሪያን የነጻነት ቀን በዓል አስመልክተው ለመሪው ኪም ጆንግ ኡን የእንኳን አደረሳችሁ ደብዳቤ ጽፈዋል።
በደብዳቤው ሁለቱ ሃገራት "በጋራ አጠቃላይ እና ገንቢ የሁለትዮሽ ግንኙነቶቻቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ" መግለጻቸውን የኮሪያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ይበልጥ ሊያጠናክሩት የሚፈልጉት ግንኙነት በሃገራቱ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን በደብዳቤያቸው የገለጹት ፑቲን ይህ መሆኑ በኮሪያ ልሳነ ምድር፤ በሰሜን ምስራቃዊ እስያ ቀጣና ጭምር ያለውን ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ ለማጠናከር ሊረዳ ይችላል ብለዋል።
በዓሉ ኮሪያ ከጃፓን አገዛዝ ነጻ የወጣችበትን ቀን በዓል ለማስታወስ በየዓመቱ በፈረንጆቹ ነሐሴ 15 ይከበራል።
ሆኖም ሁለቱም ኮሪያዎች በተለያየ ቀን ነው የሚያከብሩት። በሰሜን ኮሪያ ዛሬ ለ77ኛ ጊዜ በወታደራዊና በተለያዩ ሌሎች ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው።
ጃፓን ከ1910 እስከ 1945 ድረስ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ገዝታለች። ሆኖም አሜሪካን፣ ብሪታኒያን፣ ሶቪየት ህብረትን እና ቻይናን ያካተተው ጥምረት ( አላይድ ፓወር) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተቀዳጀውን ወታደራዊ ድል ተከትሎ አገዛዟ ሊያበቃ ችሏል።