ደቡብ ኮሪያ ለሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ዋና አስተዳዳሪ ምህረት አደረገች
ቢሊየነሩን ሊ ጄ ያንግ ከፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ነው ምህረቱን ያገኙት
አስተዳዳሪው ፈጽመውታል በተባለው ሙስና ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወሳል
ደቡብ ኮሪያ ለቢሊየነሩ የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ወራሽ እና ዋና አስተዳዳሪ ሊ ጄ ያንግን ምህረት አደረገች።
የግዙፉ የዓለማችን ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ባለቤት ሊ ጄ ያንግ ከፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ነው ምህረቱን ያገኙት።
በቀድሞዋ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጊዩን ሃይ የስልጣን ዘመን ፈጽመውታል በተባለው የሙስና ቅሌት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
አንዱን ዓመት በእስር ያሳለፉም ሲሆን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ለመታረም ቃል በመግባት ከእስር ቤት ወጥተው ነበር። የተፈረደባቸው የእስር ጊዜም ከሳምንት በፊት ተጠናቋል። ሆኖም የክስ መዝገባቸው ሙሉ በሙሉ አልተዘጋም። በክሱ ያጡትን ሙሉ መብት እና ነጻነት መልሶ ለማግኘት ምህረትን ማግኘት የግድ ይላቸው ነበር።
ይህን ተከትሎም ከፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ምህረት ተሰጥቷቸዋል። ፕሬዝዳንታዊ ምህረቱ
ከሶስት ቀናት በኋላ የሚከበረውን የሃገሪቱን የነጻነት በዓል አስመልክቶ የተሰጠ ነው።ሌሎች 1 ሺ 691 ገደማ እስረኞችም የፕሬዝዳንት ዮል ምህረት አግኝተዋል።
ሊ ጄ ኩባንያቸው የቻይናን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያዎች ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ነው ምህረቱን ያገኙት።
በጥሩ ተወዳዳሪነቱ ለመቀጠል የሚያስችል አመራርን ሊሰጡ ይችላሉ በሚል ምህረቱን ስለማግኘታቸውም ተነግሯል።
ሃገሪቱ የገጠማትን ምጣኔ ሐብታዊ ጫና ለማቅለልና በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ እርምጃዎችን እንዲወስዱም ስለመታዘዛቸውም የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ደቡብ ኮሪያ ለሃገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ ግንባታ የጎላጰአበርክቶ ላላቸው የቢዝነስ ሰዎች በእንዲህ ዐይነት መንገድ ምህረት የማድረግ ልምድ እንዳላትም ተነግሯል።