ደቡብ ኮሪያ እስከ ሴኡል የዘለቁትን የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች መታ ባለመጣሏ ይቅርታ ጠየቀች
የሀገሪቱን መከላከያ የወቀሱት ፕሬዚዳንት የን ሱክ የል በድሮን ላይ ያተኮረ ወታደራዊ ክንፍ እንደሚደራጅ ተናግረዋል
አምስት የፒዮንግያንግ ድሮኖች ደቡብ ኮሪያ ገብተው ለአምስት ስአታት የመቆየታቸውና ወደ ፒዮንግያንግ የመመለሳቸው ጉዳይ የሴኡልን የአየር መከላከያ ስርአት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት የን ሱክ ዮል የሀገሪቱ ጦር የሰሜን ኮሪያ ድሮኖችን መቶ ባለመጣሉ ወቀሱ።
ፕሬዚዳንቱ ድሮን ላይ ትኩረቱን ያደረግ ወታደራዊ ክንፍ እንደሚደራጅም ነው ያስታወቁት።
አምስት የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች በትናንትናው እለት የደቡብ ኮሪያን ድንበር ጥሰው በመግባት ሴኡልን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ከአምስት ስአት በላይ ቆይታ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ደቡብ ኮሪያ በተዋጊ ጄቶቿ ድሮኖቹ ወደመጡበት እንዲመለሱ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ብትከፍትም ድሮኖቹ ሳይመቱ ወደ ፒዮንግያንግ መመለሳቸውም የሴኡልን የአየር መከላከያ ስርአት ትችት እንዲበዛበት አድርጓል።
ከ100 በላይ የማስጠንቀቂያ ተኩሶችን የተኮሰው የሀገሪቱ አየር ሃይልም ይቅርታን ለመጠየቅ ተገዷል።
3 ሜትር ርዝማኔ ያላቸውን አነስተኛ ድሮኖች መቶ ለመጣል ከባድ እንደሆነበትም ገልጿል።
“ጉዳዩ የሚያስቆጭ ቢሆንም ድሮኖቹን ለመጣል ከባድ ጥቃት ያልፈጸምነው በንጹሃን ዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትንም ታሳቢ በማድረግ ነው” ብለዋል ካንግ ሺ ቹል የተባሉ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ።
ፕሬዝዳንት የን ሱክ የል ግን “ሁኔታው የአየር ሃይላችን የዝግጁነት ማነስ ያሳያል” ነው ያሉት።
የትናንቱ ተግባር የዝግጁነታችን መጠን ማሳደግ እንደሚገባን አስተምሮናል ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ በካቢኔ ስብሰባ ወቅት ባደረጉት ንግግር የቀደሙትን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ሙን ጃይ ኢንንም ወቅሰዋል። ሙን በሰሜን ኮሪያ ዙሪያ የተከተሉት ፖሊሲ ፒዮንግያንግን የልብ ልብ ሰጥቷል የሚል እምነትም አላቸው።
አዲስ የሚደራጀው የድሮን ጉዳዮችን የሚመለከት ወታደራዊ ክፍልም የስለላ ስራዎችን በሚገባ የሚከውንና ድንበር ዘልቀው ጉዳት ሳያደርሱ ፈጣን እርምጃ የሚወስድ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ በ2017 ወደ ደቡብ ኮሪያ የላከቻት ድሮን በድንበር አካባቢ ተራራ ላይ ተሰባብራ መገኘቷ ይታወሳል።
የመንግስታቱ ድርጅትን ማዕቀቦች የሚቆጣጠር ተቋም በ2016 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ሰሜን ኮሪያ ከ300 በላይ የጦር እና የሰለላ ድሮኖች አሏት።
በደቡብ ኮሪያ በ2014 እና 2014 ወድቀው የተገኙት ድሮኖችም ከአሜሪካ፣ ቻይና ጃፓን፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስዊዘርላንድ በገቡ ግብአቶች የተገጣጠሙ ስለመሆናቸው ያሳያል ነው ያለው ሪፖርቱ።
ለድሮን ቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት የሰጡር የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን፥ ፒዮንግያንግ እስከ 500 ኪሎሜትሮች የሚጓዙ ድሮኖችን ትሰራለች ሲሉ መደመጣቸውንም ሬውተርስ በዘገባው አውስቷል።