አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ድንበር አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ አካሄዱ
ሰሜን ኮሪያ ለስድስት ቀናት የተካሄደውን ወታደራዊ ልምምድ የወረራ ዝግጅት ነው በሚል ተቃውማለች
ፒዮንግያንግ 2024 በኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት የሚቀሰቀስበት አመት ሊሆን እንደሚችልም አስጠንቅቃለች
የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ወታደሮች በሰሜን ኮሪያ ድንበር አቅራቢያ ለስድስት ቀናት ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ፒዮንግያንግን አስቆጥቷል።
ሴኡል በዛሬው እለት የተጠናቀቀውና ሜካናይዝድ ጦሯ የተሳተፈበትን ልምምድ “ለጠላታችን ወረራ የምንሰጠው ምላሽ ዝግጁነት የተፈተነበት ነው” ብላለች።
የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ ታንኮችን ጨምሮ ከ110 በላይ ከባድ መሳሪያዎች እና የጦር አውሮፕላኖች የተሳተፉበት መሆኑንም ነው ያስታወቀችው።
በሴኡል ከ28 ሺህ በላይ ወታደሮች ያሏት ዋሽንግተንም ልምምዱ የኒዩክሌር እና ሚሳኤል ፕሮግራሟን አጠናክራ ለቀጠለችው ሰሜን ኮሪያ ተጠባቂ ጥቃት ምላሽ መስጠት እንደሚያስችል ታምናለች።
አሜሪካ ባህርሰርጓጅ እንዲሁም አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን ከአራት አስርት አመታት በኋላ ወደኮሪያ ልሳነ ምድር መላኳና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿን ማሰማራቷም ስጋቱ ከማየሉ ጋር የተያያዘ መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።
ፒዮንግያንግ ግን ጎረቤቷ “የአሜሪካ የኒዩክሌር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘን” መሆኗና “ሃላፊነት የጎደለው ጸብ አጫሪ የጦር ልምምዱ” የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ገልጻለች።
ወጣቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡንም አሜሪካ ግዙፍ የጦር መሳሪያዎቿን ወደ ሴኡል መላኳን ተቃውመው “ደቡብ ኮሪያንም ሆነ አጋሯን አሜሪካ” የሚያጠፋ የኒዩክሌር መሳሪያ ልማታቸው እንዲጠናከር ማሳሰባቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ “አዲሱን አመት በወረራ ልምምድ መጀመራቸው ምን ያህል ጦርነት በአጥንታቸው ስር ዘልቆ መግባቱን ያሳያል” ሲል የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ተጀምሮ ዛሬ የተጠናቀቀው ልምምድም 2024 በኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት ሊጀመርበት የሚችል አመት ሊሆን እንደሚችል ነው ያስጠነቀቀው።
የደቡብ ኮሪያ ባህር ሃይል በበኩሉ ከትናንት ጀምሮ የተኩስ ልምምድ መጀመሩ ተነግሯል።