የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር (ኔቶ) ቀጣይ መሪ ማን ሊሆን ይችላል?
የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልትንበርግ ስልጣናቸው ከጥቂት ወራት በኋላ እንደሚያበቃ ይጠበቃል
ኔቶን ለመምረጥ እጩዎች መታወቅ የጀመረ ሲሆን፤ በእጅ አዙር ትመራለች የምትባለው አሜሪካ እጩ አላቀረበችም
ከ73 ዓመት በፊት በ12 ሀገራት በወቅቱ ሶቪየት ህብረት የምትባለውን ሀገር ለመመከት በሚል ነበር በ12 ሀገራት የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ የተቋቋመው።
አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ፖርቹጋል፣ ብሪታንያ እና ካናዳ ደግሞ የኔቶ መስራች ሀገራት ናቸው፡፡
አሁን ላይ 30 አባል ሀገራት ያሉት ኔቶ ፊንላንድ እና ስዊድን ደግሞ ህብረቱን ለመቀላቀል በሂደት ላይ ናቸው።
የቀድሞው የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት እና የአሁኑ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልትንበርግ ስልጣናቸው ከጥቂት ወራት በኋላ እንደሚያበቃ ይጠበቃል።
በኔቶ አባል ሀገራት መካከል በሚደረግ ምርጫ የድርጅቱ መሪ የሚመረጥ ሲሆን ኔቶን ለመምረጥ እጩዎች መታወቅ ጀምረዋል።
የዩክሬን የዘር ሀረግ ያላቸው ካናዳዊቷ ክሪስቲያ ፍሪላንድ ኔቶን ለመምራት በእጩነት የቀረቡ ሲሆን አሜሪካ ከወዲሁ ለ54 ዓመቷ ካናዳዊ ድጋፏን ሰጥታለች ሲል ኒዮርክ ታየምስ ዘግቧል።
የካናዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እየገለገሉ ያሉት ፍሪላንድ የቀድሞ ያካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ጋዜጠኛ የነበሩ ሲሆን እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ፣ የሩሲያ እና ዩክሬን ቋንቋዎችን መናገራቸው ኔቶን ለመምራት ዋነኛ ተፎካካሪ ሆነው መቅረባቸው ተገልጿል።
ኔቶን ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በእጅ አዙር ትመራለች የምትባለው አሜሪካ እጩ ያላቀረበች ሲሆን የአውሮፓ ሀገራት ግን የፊታችን ሚያዝያ ለሚደረገው የኔቶ ዋና ጸሃፊ ምርጫ እጩ በማቅረብ ላይ ናቸው።
የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካጃ ካላስ፣ የስሎቫኪያ ፕሬዝዳንት ዙዛና ካፑቶቫ እንዲሁም የቀድሞ የክሮሺያ ፐሬዝዳንት እና በዋሸንግተን የክሮሺያ አምባሳደር ኮሊንዳ ግራባር ኔቶን ለመምራት ከቀረቡ እጩዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ከአውሮፓ ህብረት በህዝበ ውሳኔ መውጣቷን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የመሪነት ቦታ ላይ መጥፋቷን ለማስረት ፍላጎት ያላት ብሪታንያ ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ቤን ዋላስን እጩ አድርጋ አቅርባለች።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የኔቶ አባል ሀገራት ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አለመቋጨት ተከትሎ አሁን በሀላፊነት ላይ ያሉት የድርጅቱን ዋና ጸሃፊ ስልጣን ለሁለት ዓመት ሊያራዝሙ እንደሚችሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
አሜሪካ ግን ኔቶን አዲስ መሪ እንዲመራው ፍላጎቷ ነው የተባለ ሲሆን ለዚህ ምክንያቷ ደግሞ በ2024 የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሆነ ተገልጿል።
በአሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ የተቸራት የዩክሬን የዘር ሀረግ ያላት እና የካናዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሪላንድ ከኔቶ ዋና መቀመጫ እና ወታደራዊ ማዘዣዎች መራቋ ምርጫውን ላታሸንፍ እንደምትችል ተሰግቷል ተብሏል።