ሰሜን ኮሪያ ሁለት የባላስቲክ ሚሳዔሎች ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ አስታወቀች
ሚሳዔሉ የተወነጨፈው የአሜሪካ ም/ፕሬዝዳንት ሃሪስ ሴኡል ለመግባት አንድ ቀን ሲቀራቸው መሆኑ ከፍተኛ ስጋት ጭሯል
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታው ቶሺሮ ኢኖ ፤የፒዮንጊያንግ ድረጊት "ተቀባይነት የለውም" ሲሉ አውግዘዋውታል
ሰሜን ኮሪያ፤ ጃፓን እና ሁለቱም ኮሪያዎች ወደሚያዋስነው የምስራቅ ባህር ክልል ሁለት የባላስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፏ የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታወቀ፡፡
ሰሜን ኮሪያ የባላስቲክ ሚሳዔሉን ያስወነጨፈችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በደቡብ ምስራቅ የባህር ዳርቻ በውሃ ላይ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ካደረጉ በኋላ ነው።
የሚሳዔል ማስወንጨፉ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ ሃሙስ እለት ሴኡል ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት መሆኑ ከፍተኛ ስጋት መጫሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሚሳዔሎቹ ከሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ ሱናን ከሚባለው አካባቢ ከቀኑ 18፡10 ላይ መወንጨፋቸውንም ነው የደቡብ ኮሪያና አሜሪካ የጋራ አዛዦች የተናገሩት።
ሚሳዔሎቹ ወደ 360 ኪሎ ሜትር (225 ማይል) በመብረር 30 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ የመምዘግዘግ አቅም እንዳለቸው የገለጹት አዛዦቹ፤ የፒዮንጊያንግ ትንኮሳ የሴኡል-ዋሽንግተን ጥምረት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
"የሰሜን ኮሪያ ትንኮሳ የደቡብ ኮሪያ-አሜሪካን የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት አቅም የበለጠ ያጎለብታል እንዲሁም እና ሰሜን ኮሪያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመገለሏ ጉዳይ የበለጠ የሚያጠናክር ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሚሳዔሎቹ ማስወንጨፍ ሙከራን በተመለከተ በሰሜን ኮሪያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም ቀደም ሲል የሀገሪቱ መሪ ኩም ጆንግ ኡን “ፒዮንጊያንግ የኒውክሌር እና ሚሳዔሎች ባለቤት የመትሆነው ራሷን ካምንኛውም ጥቃት ለመከላከል ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ባላስልጣናት፤ ከሃሪስ ጉዞ ጋር ለመገጣጠም የሚደረግ ማንኛውም የሚሳዔል ሙከራ ካለ "ለኮሪያ ሪፐብሊክና ለጃፓናውያን አጋሮቻችን ደህንነት” ሲባል አሜሪካ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የጃፓን መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታው ቶሺሮ ኢኖ በበኩላቸው የፒዮንጊያንግ ድረጊት "ተቀባይነት የለውም" ሲሉ አውግዘውታል።
መከላካያ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የባለስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፍን ጨምሮ የምትወስዳቸው ተከታታይ እርምጃዎች፣ ለጃፓን፣ ለቀጣናው እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት ስጋት ፈጥረዋል" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ መሰል የባላስቲክ ሚሳዔል ሙከራዎችን ስታደረግ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ-ዮል በግንቦት ወር ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለስድስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ወደ ምስራቅ ባህር ክልሏ ለመጨረሻ ጊዜ የባላስቲክ ሚሳዔል ያስቀነጨፈችው ባሳለፍነው ወርሃ ሰኔ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በአንድ ቀን ብቻ ስምንት የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ያስቀነጨፈችበት አጋጠሚ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያ አሁን ያካሄደችው የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራ ጨምሮ የፈረንጆቹ 2022 ከገባ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ20ኛ ጊዜ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡