ሰሜን ኮሪያ ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀም ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሞከረች
“ሃውሶንግ -16ቢ” የተሰኘው ሚሳኤል ፒዮንግያንግ “በየትኛውም አለም የሚገኙ ጠላቶቿን በፍጥነትና በሃይል” እንድትመታ ያስችላታል ተብሏል
ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀሙ ሚሳኤሎች በፍጥነት የመተኮስ እና በጸረ ሚሳኤል የመመታት እድላቸው ያነሰ መሆኑ ተገልጿል
ሰሜን ኮሪያ በአይነቱ የተለየ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መሞከሯን አስታወቀች።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀመው “ሃውሶንግ -16ቢ” የተሰኘው ሚሳኤል ሲወነጨፍ በአካል ተገኝተው ተመልክተውታልም ተብሏል።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን አዲሱን የፒዮንግያንግ ሙከራ የጸጥታው ምክርቤት እገዳን የጣሰ ነው በሚል ተቃውመዋል።
ዛሬ የተሞከረው ሚሳኤል የሰሜን ኮሪያን የወታደራዊ ቴክኖሎጂ “ፍጹም የበላይነት” የሚያሳይ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያ ነው ብሏል የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኪሲኤንኤ)።
ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሉ አረሩን ለማስወንጨፍ ጠጣር ነዳጅ እንደሚጠቀም ያነሳው ዘገባው፥ ይህም ፈሳሽ ነዳጅ ከሚጠቀሙት በፈጠነ ሁኔታ የመተኮስ አቅም እንዲኖረው ያደርገዋል ብሏል።
ከዚህም ባሻገር በፀረ ሚሳኤል የመመታት አቅሙ ዝቅተኛ እንዲሆን ያግዘዋል ነው ያለው።
ሰሜን ኮሪያ ሁሉንም ታክቲካል እና ስትራቴጂክ ሚሳኤሎች እንዲሁም የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች በጠጣር ነዳጅ እንዲሰሩ ለማድረግ ውጥን ይዛ መስራት ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል።
ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀሙ አጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ስትሞክር ቆይታም ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።
ሚሳኤሎቹን ጠጣር ነዳጅ እንዲጠቀሙ የማድረጉ ሂደት ፒዮንግያንግ “በየትኛውም አለም የሚገኙ ጠላቶቿን በፍጥነት፣ በሃይል እና በትክክለኛ ኢላማ ለመምታት ያስችላል” ሲሉ ኪም ጆንግ ኡን መናገራቸውን ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ተንታኞች ግን ሰሜን ኮሪያ በአጭር ጊዜ ሁሉንም ሚሳኤሎቿን ጠጣር ነዳጅ እንዲጠቀሙ ማድረግ የምትችል አይመስልም ይላሉ።
አረር ለማስወንጨፍ ፈሳሽ ነዳጅ የሚጠቀሙት እንደ “ሃውሶንግ-17” እና “ሃውሶንግ - 15” ያሉ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆንም ግልጸ አይደለም።
ሰሜን ኮሪያ ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካና አጋሮቿ የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ በመቃወም የሚሳኤል ሙከራዋን አጠናክራ ቀጥላለች።