ፒዮንግ ያንግ አዲስ ፀረ-አውሮፕላን ሮኬት ሙከራ ማድረጓም ተገልጿል
ሰሜን ኮሪያ እጅግ ግዙፍ የሆነ አዲስ ጦር መሳሪያ እና አዲስ ፀረ-አውሮፕላን ሮኬት ሙከራ ማድረጓን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፒዮንግ ያንግ ሙከራ ያደረገችበት አዲሱ ግዙፍ ጦር መሳሪያ ለስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳዔሎች የሚውል መሆኑንም የሰሜን ኮሪያ የመንግስት ሚዲያ ዘገባ ያመለክታል።
የሰሜን ኮሪያ የሚሳዔል አስተዳዳሪ ተቋም ለ"ሃውሳልl-1 አር.ኤ-3" ስትራቴጅካዊ የክሩዝ ሚሳኤል ተብሎ የተነደፈ እጅግ በጣም ትልቅ የጦር ሃይል ሙከራ ማድረጉም ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም ሰሜን ኮሪያ ትናንተ አርብ ከሰዓት ላይ “Pyoljji-1-2” የሚል መጠሪያ የተሰጠው አዲስ ፀረ-አውሮፕላን ሮኬት ሙከራ ማድረጓ ተነግሯል።
ኬሲኤንኤ በዘገባው ተጨማሪ ዝርዝሮችን ሳይሰጥ በሙከራዎቹ “በርካታ ነገሮች ግባቸውን መትተዋል” ሲል አክሏል።
የጦር መሳሪያ ሙከራዎቹ አዲስ አይነት የጦር መሳሪያ ስርዓቶች አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሳዔል አስተዳዳሪ ተቋም እና የሌሎች የመከላከያ ሳይንስ ተቋማቱ መደበኛ ተግባራት አካል መሆናቸውም ተዘግቧል።
አዳዲስ ጦር መሳሪያ ሙከራዎቹ በአካባቢው ካሉ ሁኔታዎች ጋር የማይገናኙ መሆኑንም ኬሲኤንኤ በዘገባው አስነብቧል።
በፈረንጆቹ የመያዚያ ወር መጀመሪያ አካባቢ ላይ ሰሜን ኮሪያ የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በተገኙበት አዲስ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት ያለው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን መሞከሯ ይታወሳል።