በዩክሬን የተያዘው የሰሜን ኮሪያ ወታደር ህይወቱ ማለፉ ተነገረ
የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋም በዩክሬን ጦር የተማረከው የመጀመሪያው የሰሜን ኮሪያ ወታደር "ክፉኛ በመቁሰሉ" መሞቱን ገልጿል
ዜለንስኪ በሩሲያ ኩርክስ ክልል ከተሰማሩ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል አልያም ህይወታቸው አልፏል ብለዋል
በዩክሬን ጦር የተያዘው የሰሜን ኮሪያ ወታደር ህይወቱ ማለፉ ተነገረ።
ዮናፕ የዜና ወኪል የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋምን ጠቅሶ እንዳስነበበው ፒዮንግያንግ ወደ ሩሲያ ከላከቻቸው ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩክሬን ጦር የተማረከው ወታደር ህይወቱ አልፏል።
ወታደሩ በዩክሬን ጦር ተገድሎ ሊሆን ይችላል ቢባልም የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋም ግን "ክፉኛ መቁሰሉ" ለሞት እንዳበቃው ማረጋገጡን አስታውቋል።
በኬቭ እና ሴኡል ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ ሞስኮ ልካለች በሚል የምትወቀሰው ፒዮንግያንግ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ባለፈው ሰኞ ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ከላከቻቸው ወታደሮች ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል አልያም ተገድለዋል ማለታቸውን ቢቢሲ አስታውሷል።
የሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትብብር የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን የሚያባብስ መሆኑን መሆኑን ነው የተናገሩት።
የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ግን እስካሁን ወታደሮችን ወደ ሩሲያ መላኩን ከማረጋገጥ ተቆጥበው "ሩሲያ ባስፈለግናት ጊዜ ሁሉ ለመድረስ ዝግጁ ነን" ማለትን መርጠዋል።
ፒዮንግያንግ ተጨማሪ ወታደሮች እና ድሮኖችን ወደ ሞስኮ ልትልክ እየተዘጋጀች መሆኑን የሚያመላክቱ የደህንነት መረጃዎች እንደደረሳት ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ መግለጿ አይዘነጋም።
የዩክሬን ጦር ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሀሰተኛ የሩሲያ መታወቂያ ማዘጋጀቷንና የፊት ቀለማቸውን እንዲያጠቁሩ እያደረገች መሆኑን ገልጿል።
ይህም በውጊያ ወቅት የሚሞቱ የሰሜን ኮሪያን ወታደሮች ለመለየት አስቸጋሪ እንዳደረገው ነው ያስታወቀው።
በየካቲት 2025 ሶስተኛ አመቱን ሊይዝ በተቃረበው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፤ ሞስኮ ከ20 በመቶ በላይ የዩክሬንን ግዛት ተቆጣጥራለች።
በጦርነቱ ጅማሮ የተካሄዱ ድርድሮች ተቋርጠው ምዕራባውያን ከኬቭ ጎን፤ ሰሜን ኮሪያ እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ ከሞስኮ ጎራ ተሰልፈው ከፍተኛ ውድመት ተከስቷል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ስሎቫኪያ ያቀረበችውን የንግግር ሀሳብ እንደሚቀበሉት መናገራቸውና "የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆማለሁ" ያሉት ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለመግባት መቃረባቸው ደማ አፋሳሹን ጦርነት ሊያስቆመው እንደሚችል ተስፋ ፈጥሯል።