ሰሜን ኮሪያ በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ጎረቤቷን አስጠነቀቀች
ፒዮንግያንግ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለው ውጥረት "በአንድ ድንገተኛ ተኩስ" ወደ ጦርነት ሊቀየር መቃረቡን ገልጻለች

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ "የነጻነት ጋሻ" የሚል መጠሪያ የሰጡትን አመታዊ ወታደራዊ ልምምድ ጀምረዋል
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት በርካታ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታወቀ።
"ሃንጋሄ ከተባለ ግዛት የተተኮሱት ሚሳኤሎች ወደ ቢጫ ባህር ገብተዋል" ብሏል ጦሩ ባወጣው መግለጫ።
ፒዮንግያንግ አይነታቸው እስካሁን በውል አልታወቁም የተባሉትን ባለስቲክ ሚሳኤሎች ያስወነጨፈችው ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ልምምድ በጀመረችበት እለት ነው።
በደቡብ ኮሪያ ከ28 ሺህ በላይ ወታደሮች ያሏት አሜሪካ ከሴኡል እና ከቀጠናው አጋሮቿ ጋር በተከታታይ ወታደራዊ ልምምድን ታደርጋለች።
ዋሽንግተን ልምምዶቹ "የመከላከል ባህሪ" ያላቸው ናቸው ብትልም ፒዮንግያንግ ግን "የወረራ ዝግጅት" ነው በሚል ሚሳኤሎችን በመተኮስ ቁጣዋን ትገልጻለች።
ዛሬ የተጀመረው "የነጻነት ጋሻ" የሚል ስያሜ የተሰጠው አመታዊ ወታደራዊ ልምምድ ለ10 ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፥ ከ19 ሺህ በላይ ወታደሮች ይሳተፉበታል።
በነዚህ ቀናት 16 ግዙፍ የጦር ልምምዶች እንደሚደረጉ ያስታወቀው የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፥ የሀገራቱ የጦር ጄቶች በተኩስ የሚያደርጉት ልምምድ ግን አይካሄድም ብሏል።
የደቡብ ኮሪያ አየር ሃይል አውሮፕላኖች ከሰሞኑ ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር ልምምድ ሲያደርጉ በሰሜን ኮሪያ ድንበር በሚገኝ መንደር ላይ በስህተት 8 ቦምቦችን በመወረወራቸው 31 ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል።
በዚህም ሀገራቱ በልምምድ ወቅት የሚፈጸም ተኩስ በጊዜያዊነት እንዲቆም መስማማታቸውን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የኒዩክሌር ሃይል ባለቤቷ ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ የጀመሩትን ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ "ጸብ ቆስቋሽ" ነው በሚል ተቃውማዋለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ልምምዱ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን ውጥረት ወደ ከፋ ደረጃ የሚያስገባ ነው፤ በአንድ ድንገተኛ ተኩስ ወደ ጦርነት ልንገባ እንችላለን" ማለቱን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ሁለቱ ኮሪያዎች ከ1950 - 1953 ያደረጉትን ጦርነት በተኩስ አቁም ቢቋጩም እስካሁን ድረስ የሰላም ስምምነት አልተፈራረሙም።