የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መመንተፋቸው ተገለጸ
መንታፊዎቹ ከመዘበሩት ገንዘብ ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላሩን በካሽ አውትተዋል ተብሏል

ሰሜን ኮሪያ ለዛሩስ የተሰኘ የጠላፊ ባለሙያዎች ቡድን እንዳላት ይገለጻል
የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መመንተፋቸው ተገለጸ፡፡
የእስያዋ ሰሜን ኮሪያ ላዛሩስ የተሰኘው የጠላፊ ባለሙያዎች ስብስብ የሙሉ ጊዜው ገንዘብ መመንተፍ ዓለማው ያደረገ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡
ይህ ቡድን የምዕራባዊን ሀገራት ተቋማትን ኢላማ በማድረግ ገንዘብ መመንተፍ ኢላማውን ያደረገ ሲሆን በየዓመቱ ለሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሏል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ይህ የባለሙያዎች ቡድን ባይቢት በተሰኘ የምናባዊ ገንዘብ ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ ኩባንያ ላይ የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ምዝበራ ፈጽሟል፡፡
ቡድኑ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም 300 ሚሊዮን ዶላሩን በካሽ በማውጣት መጠቀሙን ቢቢሲ የባይቢት ኩባንያ ሀላፊዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
የሙሉ ጊዜ ስራው ገንዘብ መመንተፍ ነው የተባለው ይህ ቡድን በዓለም ላይ ካሉ አደገኛ እና አስፈሪ ጠላፊዎች መካከል አንዱ ነውም ተብሏል፡፡
ገንዘቡ የተመዘበረበት ቤቢት የክሪፕቶ ኩባንያ ገንዘቡ ወጪ እንዳይደረግ እና ለማገድ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ቢሆንም እስካሁን ይህ አልተሳካለትም፡፡
አሜሪካ እና አጋሮቿ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሞቿን በበይነ መረብ ምንተፋ አማካኝነት በሚገኝ ገቢ እየደጎመች ነው የሚል ክስ በተደጋጋሚ ያቀርባሉ፡፡
ላዛሩስ የተሰኘው ይህ ቡድን ከ2019 ጀምሮ የባንክ ተቋማትን፣የክሪፕቶ ከረንሲ ኩባያዎችን እና ሌሎች ገንዘብ የሚገኝባቸውን ተቋማት ሁሉ ያጠቃል፡፡
አሜሪካ ከአምስት ዓመት በፊት በዚህ የጠላፊ ቡድን ላይ የእስር ትዕዛዝ ያወጣች ቢሆንም የቡድኑ አባላት ከሰሜን ኮሪያ ውጪ የማይንቀሳቀሱ በመሆናቸው ማሰር አልተቻለም ተብሏል፡፡