ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ላይ “ከባድ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት ዛተች
ፒዮንግ ያንግ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በካምቦዲያ ካደረጉት የሶስትዮሽ ስብሰባ በኋላ የመጀመሪያ መግለጫ አውጥታለች
ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ላይ ከባድ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በመዛት ቁጣዋን ሚሳኤል በማስወንጨፍ አሳይታለች
ሰሜን ኮሪያ አጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ ገልፃለች።
ሚሳኤሉ ወንሳን ከተሰኘችው የሀገሪቱ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ ወደ ባህር እንደተወነጨፈ ነው የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቾይ ሰን ሁይ አሜሪካን ያስጠነቀቁበትን መግለጫ ካወጡ ከጥቂት ስአት በኋላ ነው።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ባለፈው ሳምንት በካምቦዲያ ካደረጉት የሶስትዮሽ ስብሰባ በኋላ የመጀመሪያ አቋሟን ያንፀባረቀችው ሰሜን ኮሪያ የዋሽንግተን በቀጠናው እጅ መርዘምን ተቃውማለች።
በካምቦዲያው የሶስትዮሽ ስብሰባ አሜሪካ ሁለቱን አጋሮቿን ከሰሜን ኮሪያ ለመጠበቅ ኒውክሌር እስከማስታጠቅ ቃል ገብታለች።
ሀገራቱ የሚያደርጉት የጦር ልምምድም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መናገራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ሰን ሁይም የሶስትዮሽ ምክክርም ሆነ የጦር ልምምድ የወረራ ዝግጅት ነው ብለውታል።
ይህ የወረራ ዝግጅታቸው ግን ይዞባቸው የሚመጣውን ከባድ ስጋት አይቋቋሙትም ሲሉም ዝተዋል። የኮሪያ ልሳነ ምድርን እያወከች ነው ባለቻት አሜሪካ ላይም ሀገራቸው ከባድ እርምጃ እንደምትወስድ ነው ያስጠነቀቁት።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ከጎረቤቷ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመመከት ወታደራዊ ሀይሏ በተጠንቀቅ እንደሚገኝ አስታውቃለች።
ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ያስወነጨፈችው የሚሳኤል ሙከራ ከስምንት ቀናት በኋላ የተደረገ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አከታትላ የሞከረቻቸው የአጭርና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች በአምስት አመት ውስጥ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዋን መጠቀሟ አይቀሬ መሆኑን ያሳያል የሚሉት አሜሪካና አጋሮቿ በጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተጠምደዋል።