ሰሜን ኮሪያ ባህር ሰርጓጅ የባሊስቲክ ሚሳይል በወታደራዊ ሰልፍ ይፋ አደረገች
አዲሱ ሚሳይል ይፋ የሆነው ኪም ዘመናዊ ሚሳይሎችን የመስራት መርሃ ግብር እንደሚጀመር ከገለጹ በኋላ ነው
“አሜሪካ በማንም ብትመራ የፀረ-ሰሜን ኮሪያ ፖሊሲዋ ስለማይቀየር የከባድ መሳሪያ ስራችን ይቀጥላል” ኪም
ሰሜን ኮሪያ ከባህር ሰርጓጅ መርከብ ላይ የሚተኮስ ያለችውን ሚሳይል ይፋ በማድረግ የፖለቲካ ስብሰባ ማብቂያዋን ባልተለመደ መልኩ አክብራለች፡፡
‘ኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ (ኬ.ሲ.ኤን.ኤ)’ የተሰኘው የሀገሪቱ መንግስት ሚዲያ ባወጣቸው ምስሎች የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በምሽት የተካሄደ ወታደራዊ ሰልፍ አሳይቷል፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በወታደራዊ ሰልፉ ወቅት
የሚዲያው ርዕሰ ጉዳይ አዲሱ ከባህር ሰርጓጅ መርከብ ይተኮሳል የተባለው ባሊስቲክ ሚሳይል እንደነበር የዘገበው ሲኤንኤን የሰሜን ኮሪያው ሚዲያ ኬሲኤንኤ ሚሳይሉ “የዓለም ከባዱ መሳሪያ” መሆኑን ስለመግለጹ አንስቷል፡፡ ከባህር ሰርጓጅ መርከብ ተተኳሹ ሚሳይል በተጨማሪ ፣ ፒዮንግያንግ ለየት ያለአዲስ የአጭር ርቀት ባሊስቲክ ሚሳይል አሳይታለች፡፡
ወታደራዊ ሰልፉ የተካሔደው ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ኃይል ያለው ሰርጓጅ መርከብ ፣ ታክቲካዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን እና የሚሳይል መከላከያ ስርዓቶችን ዘልቀው መግባት የሚችሉ የተራቀቁ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን የመስራት መርሃ ግብር እንደምትጀምር ኪም ከተናሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው፡፡
የኪም ዕቅዶች እና ለእይታ የቀረቡት ሚሳይሎች ፣ ለወደፊቱ በፒዮንግያንግ እና በመጪው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መካከል ሊኖር የሚችል የትጥቅ ማስፈታት ድርድር አሳሳቢ እንደሚሆን ማሳያ ምልክቶች መሆናቸውን ተንታኞች ተናግረዋል፡፡
ኪም ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር “የአሜሪካ መሪ ማንም ይሁን ማን ፣ እውነተኛው ተፈጥሮ እና የፀረ-ሰሜን ኮሪያ ፖሊሲ መንፈስ በጭራሽ አይለወጥም ፡፡ የኑክሌር መሳሪያዎች ስራችንም ያለማቋረጥ ወደ ፊት ይቀጥላል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ትናንት ጥር 07 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው ወታደራዊ ሰልፍ ፣ የስምንተኛው የሰራተኞች ፓርቲ ኮንግረስ ስብሰባ መደምደሚያን ለማክበር ነው፡፡