ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያን ሙዚቃ የተመለከቱ ታዳጊዎችን በ12 አመት የጉልበት ስራ ቀጣች
ፒዮንግያንግ ዜጎቿ የሴኡልን ሙዚቃና ፊልም እንዳይመለከቱ በጥብቅ ትከለክላለች
ሁለቱ ኮሪያዎች ከ70 አመት በፊት ያካሄዱትን ጦርነት በተኩስ አቁም ቢቋጩም እስካሁን የሰላም ስምምነት አልደረሱም
ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያን ሙዚቃ የተመለከቱ ታዳጊዎችን በ12 አመት የጉልበት ስራ መቅጣቷ ተነገረ።
ከሰሜን ኮሪያ ከድተው የወጡ ሰዎች ላይ የሚሰራ ድርጅት የደቡብ ኮሪያን ፊልምና ሙዚቃ በመመልከታቸው የ12 አመት ከባድ የጉልበት ስራ ቅጣት የተጣለባቸውን ሁለት ታዳጊዎች የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።
ሳንድ የተባለው ተቋም በለቀቀው ምስል የ16 አመት ታዳጊዎቹ በፒዮንግያንግ በትምህርት ቤት ተማሪዎች በተሰበሰቡበት ቅጣቱ ሲተላለፍባቸው ይታያል።
የተቋሙ ዳይሬክተርና በፈረንጆቹ 2001 ከሰሜን ኮሪያ ከድተው የወጡት ቾይ ዮንግ ሁይ እንደሚሉት፥ በታዳጊዎቹ ላይ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎች በተሰበሰቡበት ትምህርት ቤት የተላለፈው ቅጣት ሌሎች ተማሪዎችን ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው።
ስማቸው ያልተጠቀሰው ተማሪዎች ለሶስት ወራት የደቡብ ኮሪያን ሙዚቃና ፊልሞች በመመልከታቸውና ለጓደኞቻቸው በማጋራታቸው ቅጣቱ እንደተላለፈባቸው ተገልጿል።
ሰሜን ኮሪያ የጎረቤቷን ሙዚቃና ፊልም መመልከት በጥብቅ ትከለክላለች፤ በእስራትና በከባድ የጉልበት ቅጣት እንደሚያስቀጣም በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ከ2020 ወዲህ የሴኡልን የጥበብ ስራዎች መመልከት፣ የአኗኗር ዘየ እና አነጋገራቸውን ማስመሰል የፒዮንግያንግን ባህል ይበርዛል በሚል ክልከላ ማሳለፏ አይዘነጋም።
የ12 አመት ቅጣት የተላለፈባቸው ሁለቱ ታዳጊዎችም የደቡብ ኮሪያን የልብስ እና የጸጉር አሰራር መከተላቸውን ቪዲዮው ያሳያል።
በ2024 የመጀመሪያውን የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው ሰሜን ኮሪያን ከጎረቤቷ ጋር ለመዋሃድ የምታደርገውን ጥረት በይፋ ሰርዛ ሴኡልን በጠላትነት ፈርጃለች።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በኮሪያ ልሳነ ምድር “በየትኛውም ጊዜ ሊጀመር ለሚችል ጦርነት” ጦራቸው ዝግጅቱን እንዲያፋጥን ማሳሰባቸውም ውጥረቱን አባብሶታል።
ሁለቱ ኮሪያዎች ከ1950 እስከ 1953 ያደረጉትን ደም አፋሳሽ ጦርነት በተኩስ አቁም ቢያቆሙትም እስካሁን ዘላቂ የሰላም ስምምነት አልተፈራረሙም።