ሰሜን ኮሪያ ትዳራቸውን የሚፈቱ ሰዎች እንዲቀጡ የሚደነግግ አዲስ ህግ ማጽደቋ ተነገረ
አዲሱ ህግ ባለትዳሮች በማንኛውም ምክንያት ትዳራቸውን የሚፈቱ ከሆነ በእስር እና በከባድ ጉልበት ስራ እንዲቀጡ ያዛል ተብሏል
የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር በአለም ላይ ያልተለመዱ በርካታ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ ይታወቃል
እያዊቷ ሀገር ሰሜን ኮሪያ ትዳራቸውን በሚፈቱ ጥንዶች ላይ በሌላ የአለም ክፍል የማይገኝ እንግዳ ህግ ተግባራዊ ማድረጓ ተሰምቷል፡፡
አዲሱ ህግ ባለትዳሮቹ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ አካላዊ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች በደሎችን ቢያደርሱም ለመፋታት እስከወሰኑ ድረስ ቅጣቱ እንደሚተላለፍባቸው ይደነግጋል፡፡
የእንግሊዙ ዘ ሰን ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን “ባለትዳሮች አጋርነታቸውን ለመበተን በመወሰን ለሰሩት ወንጀል ከፍተኛ የጉልበት ስራ ወደ ሚሰራባቸው ካምፖች እንዲላኩ ወስነዋል” ብሏል፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ፍቺ እንደ "ፀረ-ሶሻሊስት" ድርጊት ስለሚቆጠር ጥንዶቹ እስከ ስድስት ወር ድረስ በጉልበት ካምፖች ውስጥ እንዲቆዩ ወስነዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገሪቱ ተግባራዊ ሲደረግ በነበረው ህግ በመጀመሪያ ፍቺ የጠየቀው አካል ብቻ እንዲቀጣ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ነገር ግን በአዲሱ ህግ መሠረት የፍቺ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ሁለቱም ተጋቢዎች እንዲታሰሩ ደንግጓል፡፡
በባለፈው አመት መንግስት በብዛት የትዳር ፍቺ ጥያቁ የሚያቀርቡት ሴቶች መሆናቸውን ተከትሎ የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘመቻ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል አድርጎ ነበር፡፡
በርካታ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በምታስተናግደው ሀገር የትዳር ፍቺ ምጣኔን ለመቀነስ የተለያዩ ጠንካራ ህጎችን ተግባራዊ ብታደርግም ከ2020 ወዲህ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ እንደሚገኝ ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
በ2019 ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ዝግ በሆነችው ፒዮንግያንግ የኢኮኖሚ ሁኔታ በአስከፊ ሁኔታ መጓዝ ጥንዶች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ባለመቻላቸው በርካታ ትዳሮች በመፍረስ ላይ ናቸው፡፡
ከ2010 በኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሰሜን ኮሪያ በሁለቱም ጾታዎች ከ30 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች 96 በመቶዎቹ ትዳር መመስረታቸውን ያመላክታሉ፡፡
በነዚህ መረጃዎች መሰረትም ከ1000 ባለትዳሮች መካከል 9 በመቶዎቹ ትዳራቸውን የሚፈቱት በትዳር አጋራቻው በሚደርስባቸው አካላዊ ጥቃት ምክንያት ነው፡፡