አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ጀመሩ
የሶስቱ ሀገራት የባህር ሃይል ልምምድ ለሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው
ፒዮንግያንግ ከቀናት በፊት አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መሞከሯ ይታወሳል
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በዛሬው እለት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ጀምረዋል።
የባህር ሃይል የጸረ ሚሳኤል ልምምዱ በጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አማካኝ በሆነ አለማቀፍ ውሃማ ክፍል እየተካሄደ መሆኑን የደቡብ ኮሪያ ባህር ሃይል አታውቋል።
በልምምዱ ላይ የሶስቱ አጋር ሀገራት የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች እየተሳተፉ ነው ተብሏል።
የባለስቲክ ሚሳኤል ኢላማዎችን እንዴት መለየት እና መረጃ መለዋወጥ የሚያስችሉ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች ላይም ሀገራቱ ልምምድ እንደሚያደርጉ ሬውተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ የዛሬውን ልምምድ እያደረጉ የሚገኙት ሰሜን ኮሪያ “ሃውሶንግ - 18” የተሰኘ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል በሞከረች ማግስት ነው።
ዋሽንግተን የፒዮንግያንግን የሚሳኤል ሙከራዎች በተመለከተ ከራዳሮቿ የምታገኛቸውን መረጃዎች ለሴኡልና ቶኪዮ ታጋራለች።
ይሁን እንጂ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ከአሜሪካ ራዳር ስርአት ጋር በቀጥታ እርስ በርስ አልተሳሰሩም ተብሏል።
ሀገራቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምድ ግን ስጋት እንደፈጠረባት ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ይደመጣል።
ለጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውም የሚሳኤል ማስወንጨፍ ምላሽ ስትሰጥ መቆየቷ የሚታወስ ነው።
ፒዮንግያንግ ለዛሬው የሶስቱ ሀገራት የባህር ሃይል ልምምድ የምትሰጠው ምላሽም ይጠበቃል።