ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የፒዮንግያንግን ድሮኖች ከርቀት የሚለይ እና መትቶ የሚጥል ስርአት እንዳላት አስታውቃለች
ሰሜን ኮሪያ በራሷ አቅም የሰራቻቸውን ዘመናዊ ድሮኖች ሞከረች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኬሲኤንኤ) ነጭ ቀለም ያላት ድሮን የተቀመጠላትን ኢላማ ስትመታ የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።
ኢላማዋን ከመታች በኋላ ስለምትፈነዳ “አጥፍቶ ጠፊ” የሚል ስያሜ የተሰጣት ድሮን፥ የደቡብ ኮሪያን “ኬ-2” የውጊታ ታንክ የሚመስል ኢላማ ስታጋይ ታይታለች።
በምዕራባውያን ጫና የአየር ሃይሏን በሚገባ ማዘመን የተሳናት ፒዮንግያንግ በአለማችን በሚካሄዱ የተለያዩ ጦርነቶች የድሮን ሚና እያየለ መሄዱን ተገንዝባለች ይላል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ባለፈው ቅዳሜ በየብስ እና በባህር ላይ ኢላማቸውን በሚገባ ይመታሉ የተባሉ ከአራት አይነት በላይ ድሮኖችን መሞከሯንና መሪው ኪም ጆንግ ኡንም ሙከራውን መመልከታቸውንም አብራርቷል።
ኪም በዚሁ ወቅት የሰሜን ኮሪያ ጦር ጥቃት ለመፈጸምና ቅኝት ለማድረግ የሚውሉ ዘመናዊ ድሮኖችን በፍጥነት ሊታጠቅ እንደሚገባው አሳስበዋል ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ በራሷ አቅም የሰራቻቸውን ድሮኖች የሞከረችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ባለፈው ሳምንት አመታዊ ወታደራዊ ልምምድ መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
የተወሰኑ ተንታኞች ግን ፒዮንግያንግ የሞከረቻቸው ድሮኖች ከሩሲያው “ዛላ ላንሴት-3” ድሮን ጋር እንደሚመሳሰል በመጥቀስ፥ ሞስኮ ለወዳጇ የድሮን ቴክኖሎጂን እያሸጋገረች ነው ይላሉ።
ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ ጉብኝት ሲያደርጉ የድሮን ስጦታ ተበርክቶላቸው እንደነበር በማውሳትም ፒዮንግያንግ ምናልባትም በስጦታው ላይ ማሻሻያ አድርጋበት ሞክራው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስፍረዋል።
ደቡብ ኮሪያ አዲሱ የጎረቤቷ የሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላን (ድሮን) ሙከራን በቅርበት እየተከታተልኩት ነው ብላለች።
የሀገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ሊ ቻንግ ዩን፥ ሰሜን ኮሪያ ስለሞከረቻቸው ድሮኖች ዝርዝር መረጃን ባይሰጡም ሁሉንም የፒዮንግያንግ ድሮኖች ከርቀት ለይቶ የሚመታ ስርአት አለን ብለዋል።