ሰሜን ኮሪያ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ አሜሪካን አስጠነቀቀች
ፒዮንግያንግ የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ወታደራዊ ትብብር “የእስያ ኔቶ” ነው ባለች ማግስት ነው ሚሳኤሎቹን ያስወነጨፈችው
ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር የመሰረትኩትን ወታደራዊ ትብብር ለሚያውክ ማንኛውም ሙከራ አጻፋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብላለች
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ መከላከያ አስታወቀ።
ፒዮንግያንግ ለአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ “ከባድ ምላሽ” እሰጣለሁ የሚል ዛቻ ባሰማች ማግስት ነው ሚሳኤሎቹን ያስወነጨፈችው።
በ10 ደቂቃ ልዩነት የተወነጨፉት አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ወደ ሀገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አቅጣጫ መተኮሳቸውን ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች።
የመጀመሪያው ሚሳኤል 600 ኪሎሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ ቾንግጂን በተባለው አካባቢ የውሃ ዳርቻ ውስጥ መውደቁ የተነገረ ሲሆን፥ ሁለተኛው ግን 120 ኪሎሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ ሳይፈነዳ እንዳልቀረ ተገምቷል።
ሴኡል በዛሬው እለት ፒዮንግያንግ ያደረገችውን የሚሳኤል ሙከራ “ጸብ አጫሪና የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት የሚያባባስ ነው” ያለችው ሲሆን፥ ከአሜሪካ ጋር የመሰረተችውን ወታደራዊ ትብብር ለሚያውክ ማንኛውም ድርጊት ለመመከት አጻፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን “የነጻነት ጥግ” የሚል ስያሜ የሰጡትና የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ (ቲወዶር ሩዝቬልት) ጭምር የተሳተፈችበን ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ተጠናቋል።
ሰሜን ኮሪያ በትናንትናው እለት ባወጣችው መግለጫም አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር “የእስያ ኔቶ”ን የመሰለ ወትደራዊ ጥምረት እየመሰረተች ነው ስትል መውቀሷ ይታወሳል።
ደቡብ ኮሪያ ወደ ዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን እልካለሁ ማለቷን የዚህ ማሳያ አድርጋ ያቀረበችው ፒዮንግያንግ፥ አሜሪካ በኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት እንዲባባስ እያደረገች ነው በሚል ከሳለች።
የሶስትዮሽ የጦር ልምምዱ በአጋሮቿ ሩሲያ እና ቻይና ላይ ጫና ለመፍጠር ያለመ መሆኑን በመጥቀስም
እንደ ጦርነት ዝግጅት የምትመለከተው የሶስትዮሽ ወታደራዊ ልምምድ ካልቆመ “ከባድ እርምጃ” እወስዳለሁ የሚል ዛቻዋን በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያዋ (ኬሲኤንኤ) ማሰማቷ አይዘነጋም።
የዛሬው የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራም የተለመደው የቁጣ መግለጫዋ ነው ተብሏል።
ፒዮንግያንግ ከአምስት ቀናት በፊትም ባለብዙ አረር ሚሳኤል ለመጀመሪያ ጊዜ መሞከሯ ይታወሳል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ግን የኪም ጆንግ ኡን ሀገር የሚሳኤል ሙከራ በየጊዜው እየጨመረ መሄድ እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ከባለፈው አመት ጀምሮም ሰሜን ኮሪያ እና በደቡባዊ የቻይና ባህር እየተስፋፋች ነው ያሏት ቻይና ላይ ጫና ለመፍጠር በካምፕ ዴቪድ የሶስትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራርመው ተከታታይ ልምምድ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።