ሰሜን ኮሪያ ባለብዙ አረር ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን አስታወቀች
ፒዮንግያንግ በአንድ ጊዜ ሶስትና ከዚያ በላይ የተለያዩ ኢላማዎችን የሚመታ ሚሳኤል ነው ሞከርኩ ያለችው
ደቡብ ኮሪያ ግን ሰሜን ኮሪያ አየር ላይ የፈነዳባትን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ለመሸፋፈን እንጂ አዲስ ሚሳኤል አልሞከረችም ብላለች
ሰሜን ኮሪያ ባለብዙ አረር ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ እንደዘገበው አዲሱ ባለብዙ አረር ሚሳኤል በአንድ ጊዜ ሶስትና ከዚያ በላይ የተለያዩ ኢላማዎችን የሚመታ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተሞከረው ሚሳኤል የደቡብ ኮሪያና አሜሪካን የሚሳኤል መቃወሚያዎች አልፎ ጥቃት ለማድረስ የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር የጀመረው ጥረት አካል ነው ተብሏል።
በአንድ የባለስቲክ ሚሳኤል ውስጥ ሆነው ከተተኮሱ በኋላ ወደተቀመጠላቸው ኢላማ ተበታትነው ጥቃት የሚያደርሱት ሚሳኤሎች በተሳካ ሁኔታ ኢላማቸውን መምታታቸው ተዘግቧል።
በአይነቱ ልዩ ነው የተባለው ሚሳኤል የት አካባቢ እንደተሞከረ ግን ፒዮንግያንግ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠችም።
ኬሲኤንኤ በበኩሉ ከአንድ ማስወንጨፊያ ሳይነጣጠሉ ተተኩሰው ወዲያው ኢላማቸውን ለመምታት የተነጣጠሉት የሚሳኤል አረሮች ሶስት የተለያዩ ኢላማዎችን መምታታቸው በራዳር ማረጋገጥ መቻሉን ዘግቧል።
ባለብዙ አረር ሚሳኤሎቹ በጠጣር ነዳጅ የሚሰሩና መካከለኛ ርቀት የሚጓዙ መሆናቸውንም ነው የጠቀሰው።
የሰሜን ኮሪያ አዲስ ሙከራ በርግጥም እውነተኛ ከሆነ የመጀመሪያው የባለብዙ አረር ሚሳኤል ሙከራዋ ይሆናል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ደቡብ ኮሪያ ግን ሰሜን ኮሪያ ትናንት አየር ላይ የፈነዳባትን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ለመሸፋፈን እንጂ አዲስ ሚሳኤል አልሞከረችም በሚል ውድቅ አድርጋዋለች።
ፒዮንግያንግ ሙከራውን ያሳያል በሚል የለቀቀችው ምስልም በመጋቢት ወር 2023 የተሞከረው ሃውሶንግ - 17 አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መሆኑን የደቡብ ኮሪያ ጦር አዛዥ ሊ ሱንግ ጆን ተናግረዋል።
“ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ይፋ ያደረገችው መረጃ የተጋነነ እና የትናንቱን ያልተሳካ ሙከራ ለመሸፈን የተደረገ ቅጥፈት ነው”ም ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሳምንት በፒዮንግያንግ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ከመከሩ በኋላ አሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቧን ወደ ሲኡል መላኳ ይታወሳል።
ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና አሜሪካ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ግንኙነቷን ላጠናከረችው ሰሜን ኮሪያ አሳሳቢ የኒዩክሌር መርሃ ግብርን ለማስቆም ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ ነው።
የሀገራቱን ጦር የጋራ ልምምድ እንደ ጦርነት አዋጅ የምትመለከተው ፒዮንግያንግ ቁጣዋን ሚሳኤል በማስወንጨፍ ስትገልጽ ቆይታለች።