ሰሜን ኮሪያ ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎችን በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን ገለጸች
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ለ11 ቀናት የሚያካሂዱትን ወታደራዊ ልምምድ ከመጀመራቸው አስቀድማ ነው ፒዮንግያንግ ሚሳኤሎቹን የሞከረችው
የሀገራቱን ወታደራዊ ልምምድ “የወረራ ዝግጅት” ነው ያለችው ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል
ሰሜን ኮሪያ ከባህር ላይ ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎችን በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን ገለጸች።
1 ሺህ 500 ኪሎሜትር የተምዘገዘጉት ሚሳኤሎች ኢላማቸውን መምታታቸውንም የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት (ኬ ሲ ኤን ኤ) ዘግቧል።
ሚሳኤሎቹ “ስትራቴጂክ” ወይም ኒዩክሌር ተሸካሚ እንደሆኑም ነው ፒዮንግያንግ ያስታወቀችው።
በትናንትናው እለት የተካሄደው ሙከራ ሀገሪቱ የባህር ላይ ጥቃቶችን የመመከት አቅሟ አስተማማኝ መሆኑን የሞከረችበት መሆኑ ተገልጿል።
- አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ የሚመጣውን ማንኛውንም የኒውክሌር አደጋ ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን አሉ
- ሰሜን ኮሪያ ተመድ የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድን እንዲያስቆም ጠየቀች
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2007 ወዲህ ግዙፍ ነው የተባለና ለ11 ቀናት የሚቆይ የጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ዛሬ ይጀምራሉ።
ይህን ልምምድ ግልጽ “የወረራ ዝግጅት” አድርጋ የምትመለከተው ፒዮንግያንግ ትናንት ክሩዝ ሚሳኤሎችን መሞከሯን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲሆን አዛለች።
“ሰሜን ኮሪያ መደበኛ ወታደራዊ ልምምዳችን ለጸብ አጫሪ ድርጊቷ እንደ ሰበብ ማንሳቷ አሳዛኝ ነው” ያሉት የደቡብ ኮሪያ የአንድነት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮ ያንግ ሳም፥ ድርጊቷ የኮሪያን ልሳነ ምድር ውጥረት ከመጨመር ውጭ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ትናንት ወደ ጃፓን የባህር ክልል የተሞከሩት ክሩዝ ሚሳኤሎች ስላደረሱት ጉዳት ቶኪዮ ምንም መረጃ አላገኘሁም ብላለች።
ሚሳኤሎቹ ሰሜን ኮሪያ እንደገለጸችው 1 ሺህ 500 ኪሎሜትር የመጓዝ አቅም ካላቸው ግን የኮሪያ ልሳነ ምድርን ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም ብለዋል የጃፓን የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባሉ ሂሮካዙ ማትሱኖ።
በቀጣይ ቀናት አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ሲያደርጉም የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ፒዮንግያንግ የባለስቲክ ሚሳኤል የምታስወነጭፍባቸው ግዙፍ የጦር መርከቦችን በስፋት እየሰራች መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ሀሙስ አጭር ርቀት የሚጓዙ ሚሳኤሎችን ስትሞክርም የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን፥ ጦራቸው ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን እንዲከላከል ብሎም ለ”ትክክለኛ ጦርነት” እንዲዘጋጅ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
በትናንትናው እለትም በአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ ዙሪያ ሊወሰዱ ስለሚችሉ ወሳኝ እርምጃዎች ፓርቲያቸውን ስብሰባ መጥራታቸው ተዘግቧል።