ፑቲን ደቡብ ኮሪያን ባስጠነቀቁ ማግስት ሴኡል የሩሲያን አምባሳደር ጠራች
ደቡብ ኮሪያ ሞስኮና ፒዮንግያንግ የተፈራረሙት የደህንነት ስምምነት ከፍተኛ ስጋት ደቅኖብኛል ብላለች
አሜሪካ እና ጃፓንም ስምምነቱ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት እንደሚያባብስ አስታውቀዋል
ደቡብ ኮሪያ በሴኡል የሚገኙትን የሩሲያ አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች።
ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ከሁለት ቀናት በፊት የተፈራረመች የደህንነት ስምምነት ደቡብ ኮሪያን አስቆጥቷል።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ጆረጂ ዚኖቬቭን በዛሬው እለት የጠራውም ሞስኮ ከፒዮንግያንግ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት እንድትሰርዝ ለማሳሰብ ነው ተብሏል።
አምባሳደሩ የሀገራቱ ስምምነት ደቡብ ኮሪያ ላይ አልያም ሌላ ሀገር ላይ በጋራ ጦር ለማስበቅ ያለመ አይደለም ቢሉም የዮን ሱክ የል አስተዳደር ግን የመንግስታቱ ድርጅትን ክልከላ የሚጥሰው ስምምነት የፒዮንግያንግን ወታደራዊ አቅም ያሳድጋል የሚል ስጋት አለው።
ፑቲን እና ኪም የተፈራረሙት በወረራና ክፉ ጊዜ የመደራረስ የትብብር ስምምነትን ተከትሎ ሴኡልም ለኬቭ የጦር መሳሪያ ልትልክ እንደምትችል መግለጿ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ፑቲንም በትናንትናው አለት በቬትናም መዲና ሀኖይ ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ የመላክ ውጥኗ "ትልቅ ስህተት" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጎረቤቷ በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎችን ለሩሲያ መላኳን የምታምነው ደቡብ ኮሪያ የፑቲንና ኪም እያደገ የሄደ ትብብር ለኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላም አስጊ ነው ብላለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ታይ ዩልም ለአሜሪካና ጃፓን አቻዎቻቸው በመደወል የመከሩ ሲሆን፥ ሀገራቱ የሞስኮና ፒዮንግያንግ ስምምነት ስጋት መደቀኑን በማመን የሶስትዮሽ ትብብራቸውን ለማሳደግ መስማማታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
አንድ ሰሜን ኮሪያዊ ወታደር በዛሬው እለት ድንበር ጥሶ ወደ ደቡብ ኮሪያ መግባቱን ተከትሎ የሁለቱ ኮሪያዎች የድንበር ውጥረት መባባሱ ተሰምቷል።
ከወደ ደቡብ ኮሪያ የኪምን አስተዳደር የሚቃወሙ መልዕክቶችን የያዙ ፊኛዎች መላካቸውም የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ እንዲያወጡ አድርጓቸዋል።