የደቡብ ኮሪያ ጦር ከሰሜን ኮሪያ ለተከፈተበት የተኩስ እሩምታ የቃል ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተሰምቷል
ሰሜን ኮሪያ ሰኞ እለት ወደ 130 የሚጠጉ መድፎችን ከደቡብ ኮሪያ ጋር በምትዋሰንበት በምዕራብ እና በምስራቃዊ የባህር ድንበሯ አቅራቢያ መተኮሷ ተሰምቷል።
ይህ ወታደራዊ እርምጃ በጎረቤቶች መካከል ያለውን የተካረረ ግንኙነት እንዲባባስ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።
የሰሜን ኮሪያ ጦር እንደተናገረው የተኩስ ልውውጡ በደቡብ ኮሪያ የድንበር ከተማ ቼርዎን አቅራቢያ እየተካሄደ ያለውን የደቡብ ኮሪያ የመድፍ ልምምድ ማስጠንቀቂያ ነው። ጦሩ ለሀገራቱ ውጥረቱ መባባስ ደቡብ ኮሪያን ተጠያቂ አድርጓል።
የደቡብ ኮሪያና የአሜሪካ የጋራ ወታደራዊ አዛዥ ሰኞ ከሰዓት በኋላ የተተኮሰው መድፍ ድንበር ውስጥ አልገባም ብለዋል።
መድፎቹ ከሰሜን ኮሪያ ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ የባህር ጠረፍ አካባቢዎች በፈረንጆቹ 2018 በኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ለመቀነስ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ በተደረገ ክልል ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል።
ቪኦኤ በደቡብ ኮሪያ ግዛት ውስጥ ጥይቶቹ ስለመውደቃቸው እስካሁን የተገኘ መረጃ የለም ብሏል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር ከሰሜን ኮሪያ ለተከፈተበት የተኩስ እሩምታ የቃል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ጠቅሶ ስምምነቱን እንድታከብር አሳስቧል።
የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ ጦር ኃይሎች የሰሜን ኮሪያን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነ የጠቀሰው ዘገባው፤ የጋራ አዛዦቹ ለማንኛውም "ሊፈጠር የሚችል አደጋ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን በማጠናከር ላይ ናቸው" ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል ብሏል።
የሰሜን ኮሪያው ተኩስ ዋሽንግተን፣ ሴኡል እና ቶኪዮ በአንዳንድ የሰሜን ኮሪያ ሰዎች እና የሀገሪቱን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እና የሚሳይል መርሃ-ግብሮችን በገንዘብ ይደግፋሉ ባሏቸው ተቋማት ላይ ተምሳሌታዊ የተባለ ማዕቀብ ከጣሉ ከቀናት በኋላ የተጸመ ነው።