ሰሜን ኮሪያ ሶስተኛውን የስለላ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራ በቀጣይ ቀናት ታደርጋለች
ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሙከራው የመንግስታቱ ድርጅትን ማዕቀብ የሚጥስ ነው በሚል አጥበቀው ተቃውመውታል
ፒዮንግያንግ ያደረገቻቸው ሁለት የስለላ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራዎች ሳይሳኩ መቅረታቸው ይታወሳል
ሰሜን ኮሪያ በቀጣይ ቀናት ሶስተኛውን የስለላ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራ እንደምታደርግ አስታወቀች።
ሙከራው ከነገ እስከ ታህሳስ 1 2023 ድረስ ባሉት ቀናት ሊካሄድ እንደሚችልም ለጃፓን መግለጿ ተጠቁሟል።
የጃፓን የባህር ዘብ ፒዮንግያንግ ሙከራውን በቢጫ ባህር እና ምስራቅ ቻይና ባህር አቅጣጫ እንደምታደርግ ማሳወቋን ነው የገለጸው።
ሶስተኛው የስለላ ሳተላይት ሙከራ የመንግስታቱ ድርጅት እገዳን የሚጥስ ነው ያሉት ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የሀገሪቱ ጸረ ሚሳኤል ስርአት ያልተጠበቀ ነገር ከተከሰተ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆን አዘዋል።
“ምንም እንኳን የሳተላይት ሙከራ ነው የሚደረገው ቢባልም የባለስቲክ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ከዋለ የመንግስታቱ ድርጅትን ክልከላ ይጥሳል” ያሉት ኪሺዳ የሀገራችን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ለሚጥል ጉዳይ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ አሳስበዋል።
ቶኪዮ ከአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር በመሆን ፒዮንግያንግ ከሶስተኛ የስለላ ሳተላይት ማስወንጨፍ ሙከራዋ እንድትታቀብ ጥረት ማድረጓን እንደምትቀጥልም ነው የተናገሩት።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴርም የሰሜን ኮሪያን የሳተላይት ማምጠቅ ሙከራ እቅድ በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
በያዝነው የፈረንጆቹ አመት ሁለት የስለላ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራ አድርጋ ያልተሳካላት ፒዮንግያንግ ሳተላይት ማምጠቅ ሊቃጣባት የሚችል ጥቃትን አስቀድማ ለመመልከት ያስችላታል።
በተለይ የደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ወታደሮች እንቅስቃሴን ለመቃኘት የስለላ ሳተላይቷ ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑ ይነገራል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በመስከረም ወር በሩሲያ ባደረጉት ጉብኝትም ይህን እውን ለማድረግ የሞስኮ እገዛ እንደማይለያቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ነግረዋቸው ነበር።
የፒዮንግያንግን የሳተላይት ማምጠቅ ሙከራ የደህንነት ስጋታችን ነው ያሉት ቶኪዮ እና ሴኡል ከዋሽንግተን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን ለመግዛት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሴኡል ከ9 ቀናት በኋላም በአሜሪካ እገዛ የመጀመሪያ የቅኝት ሳተላይቷን ለማምጠቅ ማቀዷን ሬውተርስ ዘግቧል።