ሰሜን ኮሪያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ጋር ፎቶ የተነሱ ስፖርተኞቿን ልትቀጣ ነው
ፒዮንግያንግ አትሌቶቿ ወደ ፓሪስ ከማቅናታቸው በፊት ከደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ጋር እንዳይገናኙ ጥብቅ ማሳሰብያ አስተላልፋ ነበር
አትሌቶቹ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ለጸረ ሶሻሊስታዊ እሳቤ ተጋልጠው ሊሆን ይችላል በሚል “የማንጻት” ሂደት ውስጥ ይገኛሉ
ሰሜን ኮሪያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ጋር ፎቶ የተነሱ ስፖርተኞቿን ልትቀጣ ነው
ሰሜን ኮሪያ በፓሪሱ ኦሎምፒክ ከደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ጋር ፈገግ ብለው ፎቶ የተነሱ የጠረጴዛ ቴንስ ተጫዋች አትሌቶቿ ላይ ቅጣት ልታሳልፍ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በውድድሩ የብር ሜዳሊያ ለሀገራቸው ማስገኝት የቻሉት ኪም ኩም ዮንግ እና የቡድን አጋሩ ሪ ጆንግ ሲክ የወርቅ ሜዳሊያ ካገኘችው ቻይና እንዲሁም የነሀስ ሜዳሊያ ከወሰደችው ደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ጋር ፈገግ ብለው በተነሱት “ሰልፊ ፎቶ” ምክንያት ችግር ውስጥ ገብተዋል ነው የተባለው፡፡
በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘንድ የስፖርታዊ ወንድማማችንት ማሳያ ተደርጎ በሰፊው ሲቀርብ የነበረው ይህ ፎቶ በኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ዘንድ ህግን የተላለፈ ነው ተብሏል፡፡
በዘንድሮው ኦሎምፒክ ሰሜን ኮርያን ወክለው የተወዳደሩ አትሌቶች ከተላለፉላቸው ጥብቅ መመሪያዎች መካከል ከየትኛውም የደቡብ ኮሪያ አትሌት ጋር እንዳይገናኙ የሚያዘው አንደኛው ነው፡፡
አትሌቶቹ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ “ለጸረ ሶሻሊስታዊ እሳቤ” ተጋልጠው ሊሆን ይችላል በሚል “የማንጻት” ሂደት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በሀገሪቱ የስፖርት ሚንስቴር እንደሚካሄድ የተነገረው ለአንድ ወር ይቆያል የተባለው “ከባእድ እሳቤ የማንጻት ስራ” ሶስት ደረጃዎች ሲኖሩት የርዕዮተ አለም ግምገማ ፣ ሀገሪቷ ለተገበረቻቸው ህግ እና መመሪያዎች ተገዥነትን መፈተሸ እና የጸረ ሶሻሊስታዊ እሳቤ ማጣሪያዎችን ያካትታል ነው የተባለው፡፡
አትሌቶቹ ተላልፈውታል ለተባለው መመሪያ ምን አይነት ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው እሳካሁን ግልጽ የሆነ ነገር ባይኖርም በ2010 የአለም ዋንጫ ተሳትፎ ነበረው የሀገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ደርሶበት የነበረውን አይነት ቅጣት እንደሚወሰንባቸው ይጠበቃል፡፡
በ2010 የደቡብ አፍሪካ የአለም ዋንጫ ተሳትፎ የነበረው የእግር ኳስ ቡድን ምንም ጎል ሳያስቆጥር ከውድድሩ መሰናበቱን ተከትሎ የቡድኑ አባላት ህዝብ በተሰበሰበበት ለ6 ሰአታት የረዘመ ተግሳጽ የተቀበሉ ሲሆን የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ደግሞ በጉልበት ስራ እንዲያገለግል ተወስኖበት እንደነበር ይታወሳል፡፡