ሰሜን ኮሪያ ግዙፍ የሮኬት ማስወንጨፊያዎቿን ኪም በተገኙበት ሞከረች
በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ልምምድ ሴኡልን እና ዋና ዋና ወታደራዊ ጣቢያዎችን የማፈራረስ ግብ እንዳለው ተገልጿል
ፒዮንግያንግ በትናንትናው እለት የባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል
ሰሜን ኮሪያ አዳዲስና ግዙፍ የሮኬት ማስወንጨፊያዎቿን ኪም ጆንግ ኡን በተገኙበት ሞከረች።
ልምምዱ ፒዮንግያንግ በርካታ አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ባስወነጨፈች ማግስት ነው በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴኡል መግባታቸውን ተከትሎ ከሁለት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከረችው የባለስቲክ ሚሳኤል ዋሽንግተን እና የቀጠናው አጋሮቿን ሴኡል እና ቶኪዮ አስቆጥቷል።
ኪም በጣም ግዙፍ የሆኑ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች የተኩስ ልምምድ ሲያደርጉ መገኘታቸውም ለሀገራቱ ግልጽ መልዕክት ያስተላለፉበት ነው ተብሏል።
“ባለ600 ሚሊሜትር ሮኬት ማስወንጨፊያዎቹ ለትክክለኛ ጦርነት ብቁ መሆናቸው ተፈትሿል” ያለው የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኪሲኤንኤ)፥ ኪም በቅርብ ርቀት ሆነው ሙከራውን ሲመለከቱ የሚያሳይ ቪዲዮም ለቋል።
ኪም የሀገራቸው ጦር በኮሪያ ልሳነ ምድር በየትኛውም ጊዜ ሊነሳ ለሚችል ጦርነት ዝግጁ እንዲሆን አዘዋል።
በቅርቡ በተለያዩ የጦር መሳሪያ ማምረቻዎች በሚያደርጓቸው ጉብኝቶችም ዝግጁነቱ እንዲፋጠን ማሳሰባቸው ተዘግቧል።
በምዕራባዊ ሰሜን ኮሪያ የተደረገው የተኩስ ልምምድም የደቡብ ኮሪያን መዲና ሴኡል እና ዋና ዋና ወታደራዊ ጣቢያዎችን የማፈራረስ ግብ እንዳለው ኪም ለወታደሮች መናገራቸውን ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ ከሴኡል ጋር የተፈራረመችውን የወታደራዊ ስምምነት እና የውህደት ፖሊሲዋን መሰረዟ ይታወሳል፤ የሁለቱ ኮሪያዎች ውህደትን የሚያሳዩ ሀውልቶች እንዲፈርሱ ማዘዛቸውም አይዘነጋም።
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የምታደርገውን የጦር ልምምድ የወረራ ቅድመ ዝግጅት አድርገው የሚመለከቱት ኪም ጆንግ ኡን፥ ለማይቀረው ጦርነት መዘጋጀት የመረጡ ይመስላል።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የጎረቤቷ የሚሳኤል ማስወንጨፍና የተኩስ ልምምድ አደገኛ የጦርነት ጉሰማ መሆኑን ትገልጻለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሺን ዎን ሲክም “ፒዮንግያንግ በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ ካስወነጨፈች ጦርነት እንዳወጀች ይቆጠራል፤ ጠንካራ አጻፋዊ ምላሽ ያስከትላል” ብለዋል።