ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ ክምችት በሚገኝበት ድንበር የሚገኘውን ሁለቱን ኮሪያዎች የሚያገናኘውን መንገድ ማፍረሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል
ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያገናኛትን መንገድ ማፍረሷ ተነገረ።
ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ ክምችት በሚገኝበት ድንበር የሚገኘውን ሁለቱን ኮሪያዎች የሚያገናኘውን መንገድ ማፍረሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር በዛሬው እለት አስታውቋል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር ባወጣው መግለጫ ሁለቱን ሀገራት ከሚለየው ወታደራዊ መስመር በስተሰሜን በኩል ያለው መንገድ አንደወደመ ገልጿል። ጦሩ በምላሹ የቅኝት እና ዝግጁነት እንቅስቃሴዎችን ጨምሯል።
ሴኡል በትናንትናው እለት ፒዮንግያንግ መንገዱን ለማውደም ዝግጁ ነች ስትል አስጠንቅቃ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ላይ ድሮን በማብረር መክሰሷን ተከትሎ በኮሪያ ባህረሰላጤ ያለው ውጥረት አይሏል።
ድሮኖቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው በራሪ ወረቀቶችን በትነዋል ያለችው ሰሜን ኮሪያ ድርጊቱ ወደ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ትልቅ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ትንኮሳ ስትል ገልጻዋለች። ድሮኖቹን የደቡብ ኮሪያ ጦር ወይም ግለሰቦች አብርረዋቸው እንደሆነ በትናንትናው የተጠየቁት የደቡብ ኮሪያ ጦር ቃል አቀባይ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።
የሰሜን ኮሪያው መሪ "ጠላት ለሚያደርገው ከፍተኛ ትንኮሳ እና የሰሜን ኮሪያን ሉአላዊነት የመጣስ ተግባር" የሚሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ከሀገሪቱ የመከላከያ እና የደህንነት ባለስልጣናት ጋር በትናንትናው እለት ወይይት አድርገዋል።
ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ በሽዎች የሚቆጠሩ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎችን በመላክ ከፍተኛ ውዝግ እንዲነሳ አድርጋ ነበር።
ባለፈው ታህሳስ ወር ሰሜን ኮሪያ ከ2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ድንበር በጣሰችበት ተግባር አምስት የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች የደቡብ ኮሪያን ድንበር ጥሰው መግባታቸው እና ሴኡል የጦር ጄቶቼን ለማሰማራት መገደዷ ይታወሳል።
ከ1950-53 የተደረገው የሁለቱ ኮሪያዎች የእርስ በእርስ ጦርነት በተኩስ አቁም ካበቃ በኋላ የሰላም ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት አሁንም ቅራኔ ውስጥ ናቸው።