ብራዚል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እንድታስር ዩክሬን ጠየቀች
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከአንድ ወር በኋላ በሪዮ ዲጀነሪዮ ከተማ በሚካሄደው የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ ላይ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል
የክሬሚሊን ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ፕሬዝዳንቱ እስካሁን በጉባኤው ላይ ስለመሳተፋቸው ማረጋገጫ አልሰጠም
ብራዚል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እንድታስር ዩክሬን ጠየቀች፡፡
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ ዋነኛ መሪ የሆኑት ፕሬዝዳንት ፑቲን ለላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በንጹሃን ዩክሬናዊን ላይ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ፕሬዝዳንት ፑቲን የወጣባቸውን የእስር ማዘዣ መሰረት በማድረግ የፍርድ ቤቱ ፈራሚ ሀገራት አስረው የማስረከብ ግዴታ አለባቸው ብሏል፡፡
የብራዚሏ ሪዮ ዲ ጀነሪዮ ከአንድ ወር በኋላ የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤን የምታስተናግድ ሲሆን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ድሮን እንዲመረት አዘዙ
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዚህ ጉባኤ ላይ ከተሳተፉ ብራዚል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ መሰረት ፕሬዝዳንቱን እንድታስር ዩክሬን ጠይቃለች፡፡
ብራዚል የጦር ፍርድ ቤቱ ፈራሚ ሀገር በመሆኗ የእስር ትዕዛዙን የማክበር ግዴታ እንዳለባትም ዩክሬን አሳስባለች፡፡
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ከፕሬዝዳንት ፑቲን በተጨማሪ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር እና ሌሎች ወታደራዊ መሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡
ሌላኛዋ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤቱ አባል የሆነችው ሞንጎሊያ ከአንድ ወር በፊት በፕሬዝዳንት ፑቲን የተጎበኘች ሲሆን ከዩክሬን የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ፕሬዝዳንት ፑቲን በሪዮ ዲጀነሪዮ በሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ በሚል ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን” ሲሉ መልሰዋል፡፡