ዩን ሲውክ ዬኦል ከ7 ዓመት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት የነበሩትን ፓርክ የሙስና መዝገብ መርምረው ነበር
ዩን ሲውክ ዬኦል አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።
የእስያ አህጉር አራተኛው ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳናታዊ ምርጫን አስተናግዳለች።
በዚህ ምርጫ ላይ ሁለት እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩ ሲሆን የ61 ዓመቱ የፒፕል ፓወር ፓርቲ እጩ የሆኑት ዩን ሲውክ ዬኦል አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዘዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
በጥብቅና ስራ ይተዳደሩ የነበሩት ዩን የገዢው ፓርቲ እጩ የሆኑትን ሊ ጃኢ ሚዩንግን በጠባብ ውጤት አሸንፈዋል ሲል የደቡብ ኮሪያ ዜና አገልግሎት ዮናፕ ዘግቧል።
አዲስ የተመረጡት ፕሬዚዳንት ዩን በፈረንጆቹ 2017 በስልጣን ላይ የነበሩት ፓርክ ጆንግ ሄ በሙስና እንዲከሰሱ እና በፍርድ ቤት እንዲቀጡ ምርመራውን በመምራት ትልቁን ሃላፊነት መወጣታቸው በደቡብ ኮሪያዊያን ዘንድ እንዲመረጡ አድርጓቸዋልም ተብሏል።
በምርጫው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት መራጮች መካከል 98 በመቶዎቹ ድምጽ የሰጡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 48 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ለዩን ሲውክ ዬኦልን መርጠዋል።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት በሁለት ወራት ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ ሚሳኤል ያስነጨፈችው ጎረቤት አገር ሰሜን ኮሪያ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል እንደሚጠበቅበት የአገሪቱ ዜጎች ተስፋ አድርገዋል ተብሏል።
52 ሚሊየን የህዝብ ብዛት ያላት ደቡብ ኮሪያ ኦሚክሮን በተሰኘው አዲስ ልውጥ የኮሮና ቫየረስ ከተጠቁ የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ናት።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንትም በኮሮና ቫይረስ የተጎዳውን የአገሪቱ ኢኮኖሚን የሚያሻሽሉ እርምጃዎች እና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መቀነስና መከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን መስራትም ይጠበቅባቸዋል፡፡
አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዘዳንት ሙን ጃኢን ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉ ሲሆን በወራት ውስጥ ለአዲ ተመራጭ ፕሬዘዳንት ዩን ሲውክ ዬኦል ስልጣን እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል፡፡