ሰሜን ኮሪያ በየትኛውም የአለም ክፍል ጥቃት ማድረስ የሚችል ሚሳኤሏን አሳየች
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከሴት ልጃቸው ጋር የታደሙት ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት ተካሂዷል
ፒዮንግያንግ ያሳየችው ግዙፍ ወታደራዊ ትርኢት መልዕክቱ ለአሜሪካ ነው ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ የአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤሎቿን በስፋት ያሳየችበት ትርኢት ታይቷል።
ወታደራዊ ትርኢቱ ከሀገሪቱ ጦር 75ኛ አመት ምስረታ ጋር ተገጣጥሟል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ሴት ልጃቸው በፒዮንግያንግ የተካሄደውን ትርኢት መመልከታቸውን የሚያሳዩ ምስሎችንም የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አጋርቷል።
ሰሜን ኮሪያ በትርኢቱ 11 “ሃውሶንግ 17” የተሰኘውን አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ማሳየቷም በኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት እያባባሰች ነው ላለቻት አሜሪካ ግልጽ መልዕክት የሰደደ ነው ተብሏል።
አሜሪካን ማጥቃት የሚችሉት አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች በቁጥር በርከት ብለው በትርኢቱ እንዲታዩ መደረጉም የሀገሪቱን ወታደራዊ ዝግጁነትና የአጻፋ ምላሽ አቅም ለማመላከት ያለም ስለመሆኑ ተነግሯል ይላል የቢቢሲ ዘገባ።
ኪም ጆን ኡን በወታደራዊ ትርኢቱ እየተንቀሳቀሱ ወታደሮቻቸውን ሲያበረታቱ የሚያሳዩትን የደስታ ስሜት የሚያሳዩ ምስሎችም እየወጡ ነው።
ደቡብ ኮሪያ ግን ፒዮንግያንግ በከባድ የምግብ እጥረትና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እያለች ይህን መሰሉን ወታደራዊ ትርኢት ማሳየት ጥቅሙ አልታየኝም በሚል ተቃውማዋለች።
“ሰሜን ኮሪያ ህገወጥ የኒዩክሌር እና ሚሳኤል ፕሮግራሟን እና ዛቻዋን አቁማ ወደ ድርድር እንድትመለስ እንጠይቃለን” የሚል መልዕክትንም የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይዞ መውጣቱን ዮንሃፕ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ ግን የኒዩክሌር ፕሮግራሟ ራሷን የመከላከል ሉአላዊ መብቷን ማረጋገጫ መሆኑን በመጥቀስ አሁንም በአቋሟ ገፍታበታለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ የቀጠናው አጋሮቿን አስተባብራ ሰሜን ኮሪያ ላይ ልታደርስ የምትችለውን ጥቃት ለመመከት በሚል ወታደራዊ ዝግጁነቷን ይበልጥ እያጠናከረች እንደምትገኝ ይነገራል።
በተለይ የዋሽንግተን እና ሴኡል ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምዶች ፒዮንግያንግን ቁጣዋን በሚሳኤል እንድትመልስ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
ባለፈው አመት ብቻ ከ73 በላይ የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገውችው ሰሜን ኮሪያ በቀጣይስ ምን ትሞክራለች የሚለው የባላንጣዎቿ ስጋት ነው።