ሰሜን ኮሪያ ለመሪዋ መድሃኒት ፍለጋ ላይ ተጠምዳለች ተባለ
ኪም ጆንግ ኡን ዳግም እየጨመረ ከመጣው ክብደታቸው ጋር የተያያዙ ህመሞች እንዳሉባቸው ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች
የ40 አመቱ መሪ አባትና አያታቸው በልብ ህመም ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል
የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ለሀገሪቱ መሪ መድሃኒት ፍለጋ ላይ መጠመዳቸውን ደቡብ ኮሪያ አስታውቃለች።
ኪም ጆንግ ኡን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክብደታቸው ዳግም መጨመሩንና ከዚሁ ጋር የተያያዙ የደም ግፊትና ስኳር ህመማቸውም እየተባባሰ መሄዱን ነው የሴኡል የደህንነት መረጃዎች ያሳዩት።
ኪም በትናንትናው እለት በጎርፍ በተጠቁ አካባቢዎች ጉብኝት ሲያደርጉ ክብደታቸው በ2021 ወደነበረበት እየተመለሰ መምጣቱ ታይቷል።
170 ሴንቲሜትር ቁመት ያላቸውና 140 ኪሎግራም የሚመዝኑት ኪም ያልተመጣጠነ ክብደታቸው ከልክ በላይ የሚወስዱት አልኮልና ሲጋራ ማጨሳቸው የስኳር እና ደም ግፊት በሽታ አስከትሎባቸዋል።
የ40 አመቱ መሪ ከሶስት አመት በፊት አመጋገባቸውን በማስተካከል ክብደታቸውን በእጅጉ መቀነስ ቢችሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ክብደታቸው ወደቀድሞው መመለሱን የተለቀቁ ምስሎች አሳይተዋል።
የደቡብ ኮሪያ ዋነኛው የስለላ ተቋም “ኤንአይሲ” በትናንትናው እለት ይፋ ባደረገው መረጃ የኪም ክብደት 140 ኪሎግራም እንደሚገመትና ለከባድ የልብ ልመም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።
የስለላ ተቋሙ ለሴኡል ህግ አውጪዎች በዝግ ባደረገው ገለጻ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት በውጭ ሀገር ለመሪያቸው መድሃኒት በማፈላለግ ላይ እንደሚገኙ መናገሩንም ነው አሶሼትድ ፕረስ ምንጮቹን ጠቅሶ ያስነበበው።
በእድሜያቸው በ30ዎቹ መጀመሪያ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ ምልክት የታየባቸው ኪም አባታቸውንም ሆነ አያታቸውን ያሳጣቸው የልብ ህመም ሊያጠቃቸው እንደሚችል በስፋት ተገምቷል።
ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር በቆላለፈችው ሰሜን ኮሪያ የኪምን የጤና ሁኔታ በቅርበት ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።
ኒዩክሌር የታጠቀችውን ሀገር የሚመሩት ኪም ጆንግ ኡን የጤና ሁኔታቸው ትኩረት የሚስበው ህይወታቸው ቢያልፍ ማንን እንደሚተኩ እስካሁን አለማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።
የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኪም ጎን የማትጠፋው ሴት ልጃቸው ኪም ጁ ኤ ተተኪያቸው ልትሆን እንደምትችል አመላክቷል።
የ10 ወይም የ11 አመቷ ኪም ጁ ኤ ከ2022 ጀምሮ ሚሳኤል ሲወነጨፍም ሆነ በግዙፍ የአደባባይ በዓላት ላይ ደጋግማ ከአባቷ ጋር ታይታለች።
የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ታዳጊዋን “ተወዳጇ” እና “ክብርት” እያለ መጥራት መጀመሩና ከኪም ጋር የተገኘችባቸው 60 በመቶ ስፍራዎች ወታደራዊ መሆናቸው ተተኪነቷን ይጠቁማል ብሏል የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋም።