ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ የኑክሌር ንግግር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ተገለጸ
በፈረንጆቹ 2019 የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ትራምፕ በቬትናም በማዕቀብ ጉዳይ ያደረጉት ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል
ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጡ የኑክሌር ንግግር የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የተቀላቀሉት ዲፕሎማት ተናግረዋል
ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ የኑክሌር ንግግር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ተገለጸ።
ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ በድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው የሚመረጡ ከሆነ የኑክሌር ንግግር የማድረግ ፍላጎት እንዳላት እና አዲስ የንግግር ስትራቴጂ እያዘጋጀች እንደሆነ በቅርቡ ሰሜን ኮሪያን ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የተቀላቀሉት ዲፕሎማት ተናግረዋል።
በኩባ ሰሜን ኮሪያን በዲፕሎማትነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሪ ኢል ግዩ መክዳት አለምአቀፍ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሪ ከፈረንጆቹ 2016 ወዲህ ሰሜን ኮሪያ የከዱ ከፍተኛ ባለስልጣን ናቸው።
ሪ ከአለምአቀፍ ሚዲያዎች ጋር ባደረጉት የመጀመሪ ቃለ ምልልስ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ጃፓን ዋነኛ የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረቶች መሆናቸዉን ገልጸዋል።
ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት እየመሰረተች ያለችው ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ በመጭው ህዳር በሚካሄው ምርጫ ካሸነፉ የመደራደር ፍላጎት አላት ብለዋል ሪ።
ሪ እንደገለጹት ሰሜን ኮሪያ ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ስሟ እንዲሰረዝ፣ በጦር መሳሪያ ፕሮግራሞቿ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች እንዲነሱ እና የኢኮኖሚ እርዳታ ተጠቃሚ እንድትሆን በማለም የፒዮንግያንግ ዲፕሎማቶች ለእዚያ ሁኔታ የሚሆን ስትራቴጂ እያዘጋጁ ናቸው።
ይህ የሪ አስተያየት ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ድርድር የመሳካት እድሉ ያነሰ መሆኑን እና ወታራዊ ፍጥጫ እንደሚኖር ካስጠነቀቀች በኋላ የተሰጠ ነው።
በፈረንጆቹ 2019 የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ትራምፕ በቬትናም በማዕቀብ ጉዳይ ያደረጉት ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል። ሪ እንደሚሉት ከሆነ ድርድሩ ያልተሳካው በኑክሌር ዲፕሎማሲ ጉዳይ ልምድ በሌላቸው ወታደራዊ አዛዦች ምክንያት ነው ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያን፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ አሜሪካን ከጎኗ በማሰለፍ ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ከገቡ ውለው አድረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን በቅርቡ ሰሜን ኮሪያን በጎበኙበት ወቅት፣ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው ይቻወሳል።