አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ አመታዊ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ጀመሩ
ከ200 በላይ የሁለቱ ሀገራት የጦር አውሮፕላኖች ለአምስት ቀናት የሚያካሂዱት ልምምድም ይጠበቃል
ሰሜን ኮሪያ የሴኡልና ዋሽንግተን ወታደራዊ ልምምድ የጦርነት አዋጅ ጉሰማ ነው በሚል ትቃወመዋለች
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ አመታዊ የጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ጀምረዋል።
በትናንትናው እለት በተጀመረውና “ኡልቺ ፍሪደም ሺልድ” የሚል ስያሜ በተሰጠው ልምምድ ላይ 19 ሺህ የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ልምምዱእስከ ነሃሴ 23 2016 ይቆያል ተብሏል።
የዚህ አመታዊ የጦር ልምምድ አካል የሆነው የሀገራቱ አየር ሃይሎች ለአምስት ቀናት የሚያካሂዱት ልምምድም ይጠበቃል።
በአየር ልምምዱ ከ200 በላይ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የውጊያ ጄቶች እንደሚሳተፉ የደቡብ ኮሪያ አየር ሃይል አስታውቋል።
ልምምዱ የሰሜን ኮሪያን አውሮፕላኖች እና ክሩዝ ሚሳኤሎች እንዴት መምታት እንደሚቻል በምስለ በረራ (ሲሙሌሽን) በመታገዝ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።
በደቡብ ኮሪያ 28 ሺህ 500 ወታደሮች ያሏት አሜሪካ ምን ያህል አውሮፕላኖችን በልምምዱ እንደምታሳትፍ አልተገለጸም።
ስሜን ኮሪያ የጎረቤቷን እና የአሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የኒዩክሌር ጦርነት ለመጀመር የሚደረግ ዝግጅት ነው በሚል በተደጋጋሚ ተቃውማለች።
ሀገራቱ ልምምድ በጀመሩ ማግስት ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ቁጣዋን ስትገልጽ መቆየቷም ይታወሳል።
ትናንት ለተጀመረው የሴኡልና ዋሽንግተን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የምትሰጠው ምላሽም እየተጠበቀ ነው።
ፒዮንግያንግ ለሚሳኤልና ኒዩክሌር ፕሮግራሟ ልዩ ትኩረት ብትሰጥም አየር ሃይሏ ዘመኑን የማይዋጅ እንደሆነ ይነገራል።
አብዛኞቹ የጦር አውሮፕላኖቿም ሶቪየት ሰራሽ ሚግ ጄቶች ናቸው።
እነዚህን አውሮፕላኖች ለማዘመንና በአዲስ ለመተካት የምታደርገው ጥረት በምዕራባውያን በተጣሉባት ማዕቀቦች ምክንያት ፈተና ገጥሞታል።
በመሆኑም ከሴኡል ሊቃጣ ለሚችል ጥቃት በአጭር እና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀትን መርጣለች ይላል የሬውተርስ ዘገባ።