የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማምረታችንን እንቀጥላለን ሲሉ ዛቱ
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸግ መቀጠልን ጨምሮ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/09/243-103502-img-20250209-093135-865_700x400.jpg)
ሰሜን ኮሪያና ሩሲያ በደረሱት ስምምነት መሰረት ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ አንዳቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ያስችላቸዋል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማምረታችንን እንቀጥላለን ሲሉ ዛቱ።
አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ያደረጉትን የሶስትዮሽ ወታደራዊ ትብብር የተቹት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸግ መቀጠልን ጨምሮ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።
ኪም አሜሪካ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያ ወደ ቀጣናው መላኳና ከደቡብ ኮሪያና ጃፓን ጋር እያደረገች ያለው የጦር ልምምድና ወታደራዊ ትብብር ወታደራዊ የኃይል መዛባት የሚፈጥርና የቀጣናውን ደህንነት ችግር ውስጥ የሚጥል ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ የሀገሪቱን ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
"ሰሜን ኮሪያ አላስፈላጊ ውጥረት እንዲፈጠር አትፈልግም፤ ነገርግን የቀጣናውን ወታደራዊ የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ የአጸፋ እርምጃ ትወስዳለች" ሲሉ ኪም ጦሩ የተመሰረት ቀን ለማስታወስ በመከላከያ ሚኒስቴር ጉብኝት ባደረጉበት በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽገሩ እሽባ ጋር ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ስለኑክሌር ጦር ስጋት ሲያነሱ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን ብለዋል።
ነገርግን ኪም በጉብኝታቸው ወቅት የኑክሌር ጦር መሳሪያ አቅሟን ከማሳደግ ወደኋላ እንደማትል ገልጸዋል።
ኪም ስለዩክሬን- ሩሲያ ጦርነት ሲናገሩ "የሰሜን ኮሪያ ጦርና ህዝብ ሁለቱ ሀገራት በፈረሙት ወታደራዊ ትብብር መሰረት የሩሲያ ጦርና ህዝብ ሉአላዊነታቸውን፣ ደህንነታቸውንና የግዛት አንድነታቸውን ለማስጠበቅ የማያደርጉትን ፍትሃዊ ምክንያት ያለማወላዳት እንደግፋለን" ብለዋል።
ባለፈው ወር ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ 10ሺ ወታደሮች ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ ልትልክ እየተዘጋጀች መሆኗን የሚያሳይ ጥርጣሬ እንዳላት ገልጻ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ በትናንትናው እለት ባወጣችው ሌላ መግለጫ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ኮንና የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች።
ሰሜን ኮሪያና ሩሲያ በደረሱት የሁለትዮች ወታደራዊ ስምምነት መሰረት ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ አንዳቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ያስችላቸዋል።