ፒዮንግያንግ ግን ማዕቀብ ሳያግዳት የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራዋን ገፍታበታለች
ሰሜን ኮሪያን ከፀብ አጫሪ ድርጊቷ ለማስቆም አሜሪካና አጋሮቿ አዲስ ማዕቀብ ሊጥሉባት መሆኑ ተገልጿል።
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ፒዮንግያንግን እንዲርቅ የሚያደርጉ እርምጃዎችም ይወሰዳሉ ብላለች ደቡብ ኮሪያ።
የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን የደህንነት ባለስልጣናት በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ውይይት አድርገዋል።
በምክክሩም በኮሪያ ልሳነ ምድር የደቡብ ኮሪያ ልዩ መልዕክተኛ ኪም ጉን፥ ሰሜን ኮሪያ እለት ከእለት የኒዩክሌር ስጋትነቷ እያየለ መምጣቱን ተናግረዋል።
"ይህን ፀቦ አጫሪ ድርጊቷን በተባበረ የማዕቀብ እርምጃ ልናስቆመው ይገባልም" ነው ያሉት።
ሶስቱ ሀገራት በያዝነው ወርም ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል በሞከረች ማግስት በተለያዩ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ሀገራቱ በ2022 ብቻ ከ60 በላይ የሚሳኤል ሙከራ ያደረጠችው ፒዬንግያንግ በ2017 ወዳቆመችው የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራዋ ትገባለች የሚል ስጋት አላቸው።
አዲስ ይጣላል የተባለውም ሆነ የአመታት አሜሪካ መራሽ የማዕቀብ ናዳ ግን ሰሜን ኮሪያን ከሚሳኤልና ኒዩክሌር ፕሮግራሟ አላስቆማትም።
ቻይና እና ሩስያም በተደጋጋሚ የመንግስታቱ ድርጅትን የማዕቀብ እርምጃ መቃወማቸው አሜሪካ ከቀጠናው ሃገራት ጋር የደህንነት ትብብሯን ማጠናከር ላይ እንድታተኩር አድርጓል።
በጃካርታ የመከሩት የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን የደህንነት ሹማምንት የሶስትዮሽ ወታደራዊ ትብብርን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ሰሜን ኮሪያ የእነዚህ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ግልፅ የጦርነት አዋጅ ነው ብላ ወደ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን የማስጠንቀቂያ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።