በደቡብ ምስራቅ እስያ መንግስታት ማህበር ጉባኤ 'ሰሜን ኮሪያ' አጀንዳ ሆናለች
ደቡብ ኮሪያ፤ ዓለም በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ በአንድ ድምጽ ምላሽ መስጠት አለበት ብላለች
ጉባኤው፤ ፒዮንግያንግ የቀጠናው ስጋት ከመሆን እብድትቆጠብ አሳስቧል
በተለያዩ አንኳር አጀንዳዎች ላይ የሚመክረው የደቡብ ምስራቅ እስያ መንግስታት ማህበር ጉባኤ በካምቦዲያ መዲና ፕኖም ፔን በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ካነሷቸው አበይት አጀንዳዎች አንዱ የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ማበልጸግ መርሃ-ግብር ጉዳይ መሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዓለም አቀፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደንቦችን የሚጻረር የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሃ ግብር አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት መሪዎቹ፤ ፒዮንግያንግ የቀጠናው ስጋት ከመሆን እንድትቆጠብ እና ኒውከሌር ማበልጸጓን እንድታቆም ለተጀመሩ ንግግሮች ምላሽ እንድትሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ዩን ሱክ-ዮል ሰሜን ኮሪያ የምታደርገው ተከታታይ ቅስቀሳ እንዲሁም የኒውክሌር እና የሚሳይል አቅሟን ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከባድ ስጋት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሰሜን ኮሪያ ሌላ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤልን (ICBM) ካስወነጨፈች እና ሰባተኛውን የኒውክሌር ሙከራዋን ካደረገች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአንድ ድምጽ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ይሁን እንጅ ሰሜን ኮሪያ ራሷን ከኒውክሌር ነጻ ለማድረግ ከወሰነች የኢኮኖሚ ድጋፍ ትሻለች ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በተያያዘ ዮል እንደ ጸጥታ እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ጉዳዮችን ለመፍታት ሴኡል ከቻይና እና ጃፓን ጋር የምታደርገውን ትብብር ይበልጥ ማሳደግ እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡
ዩን የሀገራቱ መተባበር እንደ ጦርነት እና የመብት ረገጣ እንዲሁም የደህንነት ስጋቶች ለማስቀረት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋልም ብለዋል፡፡
ዩን በነገው እለተ እሁድ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ እና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በፕኖም ፔን ተገናኝተው በአንጓር ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም ይጠበቃል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ካምቦዲያ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ጉዞ አሜሪካ በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ያላትን ፍላጎት ለማሳካት የእስያ አጋሮቿን ትብብር ማስፋትን አላማ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡