አሜሪካና እና ደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያን ድሮኖች ለማደን የጋራ ልምምድ እያካሄዱ ነው
ሰሜን ኮሪያ፤ የዋሽንግተን እና ሴኡልን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ “ተንኳሽ” ስትል ታወግዘዋለች
የፒዮንግያንግ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተለያዩ ጊዜያት የሴኡልን የአየር ክልል ጥሰው ሲገቡ ታይቷል
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ሊቃጣባቸውን የሚል አደጋ ለመከላከል በሚል የጋራ ወታደራዊ ልምምድች ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
አሁን ላይ በተለያዩ ጊዜያት የደቡብ ኮሪያን የአየር ክልል ጥሰው የሚገቡትን የፒዮንጊያንግ ድሮኖች ለማደን የሚስችላቸውን ልምምድ በማድረግ ላይ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በአሜሪካ ጦር የታተሙ ፎቶዎች የሚያሳዩትም ዋሽንግተን እና ሴኡል በደቡብ ምዕራብ ደቡብ ኮሪያ በሚገኘው የአሜሪካ የአየር ጦር ሰፈር በጋራ የጸረ-አውሮፕላን ልምምድ ሲያደርጉ ነው፡፡
በፔንታጎን የተለቀቁ ምስሎችም እንዲሁ ልምምዱ ከሴኡል በስተደቡብ 275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኩንሳን አየር ሃይል ጣቢያ እየተካሄደ እንደሚገኝ ያሳያሉ፡፡
ሰልጣኝ ወታደሮቹ “ጸረ-ድሮን መሳሪያ” የተባለውን የራዲዮ ፍሪኩዌንሲ ጃመር፤ ሰው አልባ ወደ ሚመስል አውሮፕላን ሲያነጣጠሩና ፍንዳታ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ድሮኖችን አደጋ ለመቅረፍ “የፈንጅ መከላከያ ልብስ” ለብሰው አውሮፕላን ሲፈተሹም በምስሉ ላይ ይታያሉ።
ደቡብ ኮሪያ በቅርብ ጊዜ የተፈጸሙ የአየር ክልል ጥሰቶችን ተከትሎ ፒዮንጊያንግ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለማደን እቅድ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡
ለዚህም አሁን ላይ ስለ ኢላማዎች መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል የስለላ ስርዓት በመገንባትና ድሮኖችን ኢላማ ውስጥ ለማስገባት የሚያስችሉ ልምምዶች በማድረግ ላይ መሆኗ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን የጋራ ልምምድ አጥብቀው ሚያወግዙት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ፒዮንጊያንግ ለጦርነት ዝግጁ ናት ያሉት ከቀናት በፊት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ኪም ይህ ያሉት የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ሰብስበው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነበር፡፡
ሰሜን ኮሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋሽንግተን ሴኡል እያደረጉት ያለውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የቀጠናውን ሁኔታ ወደ “ቀይ መስመር” ወስዶታል የሚል ወቀሳም ስታቀርብ ትደመጣለች፡፡
የሰሜን ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ መግለጫው “የጋራ ልምምዱ የኮሪያን ልሳነ ምድር ወደ ጦር ቀጠና የመቀየር ስጋት የደቀነ ነው” ብሎታል፡፡ በተለይም አሜሪካ በቀጠናው የምታደረግው እንቅስቃሴ “ተንኳሽ” መሆኑን በመግለጽ፡፡
በተለይም የቅርቡ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲንን የደቡብ ኮሪያ ጉብኝን ፒዮንጊያንግን ያስቆጣ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ይህን ትበል እንጅ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተንኳሽ ነው የሚለውን ውንጀላ እንማትቀበለው አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ ትደመጣለች፡፡
“በሰሜን ኮሪያ ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ ዓላማ የለንም”ም ነበር ያለችው አሜሪካ በቅረቡ በዋይት ሃውስ በኩል ባወጣችው መግለጫ፡፡