ደቡብ ኮሪያ ለቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት ሹመት ሰጠች
በ2016 ፒዮንግያንግን ከድተው ሴኡል የገቡት ታይ ዮንግሆ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልን እንዲያማክሩ ምክትል ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል
ደቡብ ኮሪያ ከጎረቤቷ ከድተው ለሚገቡ ሰዎች ቤትና ሌሎች ድጋፎችን ትሰጣለች
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ለቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት ሹመት ሰጡ።
በፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የምክትል ሚኒስትርነት ሹመት የተሰጣቸው ታይ ዮንግሆ ናቸው።
ዮንግሆ በፈረንጆቹ 2016 ነበር ወደ ደቡብ ኮሪያ ከድተው የገቡት።
በለንደን በሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ ይሰሩ የነበሩት ዲፕሎማቱ ልጆቼ በሰሜን ኮሪያ “አስከፊ” ህይወት መኖር የለባቸውም፤ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኢም ጆንግ ኡን በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የሚፈጽሙት ግድያም አሳስቦኛል በሚል ነበር ከድተው ሴኡል የገቡት።
በ2020 በደቡብ ኮሪያ ፓርላማ ውስጥ ተመርጠው የገቡት ዮንግሆ፥ በዛሬው እለት በደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ሹመት ተሰጥቷቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ የቀድሞውን የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት የሰላም ውህደት አማካሪ ምክርቤት ዋና ጸሃፊ አድርገው ነው የሾሟቸው።
ተሿሚው የኮሪያን ውህደት እውን ለማድረግ ለፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የፖሊሲ ምክሮችን ይለግሳሉ ተብሏል።
ዮንግሆ በሰሜን ኮሪያ በዲፕሎማትነት፤ በደቡብ ኮሪያ ፓርላማ ደግሞ የውጭ ጉዳይና የውህደት ጉዳዮች ክሚቴ ውስጥ መስራታቸው ለተሾሙበት ሃላፊነት ትክክለኛው ሰው ያደርጋቸዋል ብሏል የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ።
ፒዮንግያንግ ግን በ2016 ከድቶ ወደ ደቡብ ኮሪያ የገባውን የቀድሞ ዲፕሎማቷን “አጭብርባሪ” ስትል ትወርፋቸዋለች። ግለሰቡ የመንግስትን ሀብት መዝረፋቸውንና በሌሎች ወንጀሎችም እንደምትፈልጋቸው ትገልጻለች።
ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ደቡብ ኮሪያ በመግባት ከፍተኛውን የመንግስት ስልጣን በማግኘት ዮንግሆ ቀዳሚው ናቸው ተብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን በተለይ በ1990ዎቹ ከተከሰተው አስከፊ ረሃብ በኋላ ወደ ደቡብ ኮሪያ መግባታቸው ይነገራል።
ሴኡል ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ለሚገቡ ሰዎች ቤት፣ የመቋቋሚያ ገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷንም አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ባለፈው እሁድ ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ወደ ጎረቤት ደቡብ ኮሪያ የዘለቁ ሰዎች አመታዊ ክብረበዓል ሲካሄድም ፕሬዝዳንት ዮን ሱል የል የሰሜን ኮሪያውያንን አኗኗር ለማሻሻል መንግስታቸው ድጋፉን እንደሚያጠናክር መናገራቸው ተጠቅሷል።
አብዛኞቹ ከሀገራቸው ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚገቡት ሰሜን ኮሪያውያን ሴቶች ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሚከዱ ወንድ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
በኩባ በሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት ሪ ኢ ኪዩ በህዳር ወር 2023 ከድተው ደቡብ ኮሪያ መግባታቸውን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት ከትናንት በስቲያ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።