ሰሜን ኮሪያ ከግንቦት ወር ጀምሮ በአጠቃላይ 2ሺህ ቆሻሻ የተሸከሙ ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ልካለች
ደቡብ ኮሪያ በድምጽ ማጉያ የምታሰራጨውን ጸረ ሰሜን ኮሪያ ፕሮፖጋንዳ አሳደገች።
ደቡብ ኮርያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በሚያዋስናት አስረኛው የድንበር አካባቢ አዲስ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ጀመረች፡፡
ሀገሪቱ በደምጽ ማጉያ የምታሰራጨውን ጸረ ሰሜን ኮሪያ ፕሮፖጋንዳ ለማሳደግ የወሰነችው ከሰሜኑ የሚላኩ ቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ነው፡፡
በትላንትናው እለት ሰሜን ኮሪያ የላከቻቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎች በደቡብ ኮርያ ዋና ከተማ ሰሜናዊ አካባቢ ላይ ሲያንዣብቡ ተስተውለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም 248 ኪሎሜትር በሚረዝመው ሁለቱን ሀገራት በሚያዋስነው ድንበር በአዲስ መልኩ የጀመረው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሀገራቱ የሚገኙበትን ከፍተኛ ውጥረት አመለካች ነው ተብሏል፡፡
የፕሮፖጋንዳ አይነቶቹ ኬ ፖፕ የተሰኙትን የደቡብ ኮርያ ተዋቂ ሙዚቀኞች ሙዚቃን ጨምሮ ፣ የኪም ጆንግ ኡንን አስተዳደር የሚተቹ የደቡብ ኮርያ እና የአለም አቀፍ የዜና ስርጭቶች እንደሚያካትቱ ተሰምቷል፡፡
የድምጽ ፕሮፖጋንዳ ስርጭቱ ከድንበር ጀምሮ 24 ኪሎሜትሮች ድረስ መሰማት የሚችል ሲሆን ፕሮፖጋንዳው በዚህ መጠን ሲደረግ ከ11 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በ2015 ደቡብ ኮርያ በተመሳሳይ ባደረገችው የድምጽ ማጉያ ፕሮፖጋንዳ ሰሜን ኮሪያ መድፍ በመተኮስ ምላሽ ሰጥታ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በትላንትናው እለት ወደ ሴኡል ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎቸን ስትልክ ለዘጠነኛ ጊዜ ሲሆን ከግንቦት ወር ጀምሮ በአጠቃላይ 2ሺህ ቆሻሻ የተሸከሙ ፊናዎችን ወደ ደቡብ ልካለች፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ ኮርያ ማህበረሰብ አንቂዎች ሙዚቃ፣ ፊልም፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ገንዘብ እና በራሪ ወረቀቶችን እንዲሁም ሌሎች በኪም አስተዳደር የተከለከሉ ቁሳቁሶችን ወደ ሰሜኑ እንደሚለኩ ይታወቃል፡፡
በሰሜን ኮርያ ፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያላቸው የኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህት ኪም ዮ ጆንግ ለዚህ ዮሮፖጋንዳ ጥቃት ፒዮንግያንግ ታይቶ የማይታወቅ የማያዳግም ምላሽ ትሰጣለች ሲሉ ዝተዋል፡፡
ደቡብ እና ሰሜን ኮርያ በ2018 ከፕሮፖጋንዳ እና ጠብ አጫሪ ድርጊቶች ለመታቀብ ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም በቅርብ ጊዜያት የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር የሚያደርገው ተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራ በቀጠናው ውጥረት እንዲባባስ አድርጓል፡፡