ሰሜን ኮሪያ “ጠላቶቼን ሙሉ በሙሉ ለማውደም ዝግጁ ነኝ” አለች
የሀገሪቱ ጦር የኒዩክሌር ጦርነት ለማስጀመር ባበሩ ሀገራት ላይ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ የኪም ጆንግ ኡንን ትዕዛዝ ብቻ እንደሚጠባበቅ አስታውቋል
ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ጋር ለሶስት አመት ያደረገችው ጦርነት በተኩስ አቁም የተጠናቀቀበትን 71ኛ አመት አክብራለች
ሰሜን ኮሪያ ጠላቶቿ ጦርነት ካወጁባት ወደፍርስራሽነት እንደምትቀይራቸው ገለጸች።
ኒዩክሌር የታጠቀችው ሀገር ከደቡብ ኮሪያ ጋር ተኩስ ለማቆም የተስማማችበትን 71ኛ አመት በትናንትናው እለት አክብራለች።
በዚህ በዓል ላይ የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ የእግረኛ ጦሩ አዛዥ ኮሎኔል ሪ ኡን ዮንግ እና የባህር ሃይሉ አዛዥ ሌተናል ኮማንደር ዩ ዮንግ ሶንግ ተገኝተዋል ብሏል ኬሲኤንኤ ቴሌቪዥን።
ወታደራዊ መሪዎቹ በዚሁ ወቅትም አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን “የኒዩክሌር ጦርነት ለማስጀመር እያበሩ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
ሀገራቱ ይህን ጸብ አጫሪ ድርጊታቸውን ካላቆሙና ጦርነት የሚያውጁ ከሆነ “ሙሉ በሙሉ እናወድማቸዋለን” ነው ያሉት።
ወታደራዊ አዛዦቹ “በጠላቶቻችን ላይ ያለምንም ማመንታት ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ የዋና አዛዣችን ኪም ጆንግ ኡን ትዕዛዝ ብቻ ነው የምንጠባበቀው” ማለታቸውንም ነው የሰሜን ኮሪያው ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው።
ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ጋር “ጦርነት ቀስቃሽ” ግንኙነት እየመሰረተች ነው በሚል ከምትወቅሳት አሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላትም። በ2019 ውጥረቱን ለማርገብ በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጀምሮ የነበረው ጥረትም መቋረጡ ይታወሳል።
በህዳር ወሩ ምርጫ ወደ ነጩ ቤተመንግስት የሚገባው ሰው ማንነት ከአሜሪካ ጋር አሁን ባላት ግንኙነት ላይ ምንም የሚፈጥረው ለውጥ እንደማይኖር ፒዮንግያንግ በቅርቡ አስታውቃለች።
ሰሜን ኮሪያ በፈረንጆቹ ሃምሌ 27 1953 የሶስት አመቱን የኮሪያ ጦርነት ለማስቆም ከአሜሪካ እና ቻይና ጋር ስምምነት መፈራረሟን ሬውተርስ አውስቷል።
አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የተፈራረመችው ደቡብ ኮሪያን ለመደገፍ የገባውን የመንግስታቱ ድርጅት ሃይል በመወከል ነው።
ፒዮንግያንግ የተኩስ አቁም የተፈረመበትን (ሀምሌ 27) የድል በዓል አድርጋ የምታከብረው ሲሆን፥ ሴኡል ግን ቀኑን አስባው አትውልም።
የኮሪያውን ጦርነት ያስቆመው ተኩስ አቁም ወደ ሰላም ስምምነት ባለመሸጋገሩ ሀገራቱ አሁንም ጦርነት ውስጥ እንዳሉ ይቆጠራል።