አሜሪካ እና ምዕራባውያን በዩክሬን ጦርነት በቀጥታ መሳተፍ አደጋ እንዳለው ሲገልጹ ነበር
የአሜሪካ ጦር የመረጃ መንታፊዎች ሩሲያ እና ዩክሬን እያደረጉ ባለው ጦርነት ላይ ዩክሬንን ሲያግዙ እንደነበር ተገለጸ፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ የጸጥታ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው ከሆነ አሜሪካ፤ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ መረጃን በመጥለፍ ተሳትፋለች፡፡ ብሔራዊ የጸጥታ ኤጀንሲ እና የሳይበር ኮማንድ ኃላፊ ጄነራል ፖውል ናካሶኔ የሀገራቸው መረጃ ጠላፊዎች ዩክሬን ስትከላከልና ስታጠቃ ድጋፍ ሲሰጧት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
ጄነራል ፖውል ናካሶኔ ከስካይ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ሀገራቸው በተለያየ መስክ መሳተፏ አረጋግጠዋል፡፡ የጦር መሪው እንዳሉት ከሆነ የአሜሪካ የሳይበር ቡድን በፈረንጆቹ ታህሳስ 2021 ወደ ኬቭ አምርቶ ነበር፡፡
በአሜሪካ የሚመራው የምዕራባውያን ቡድን ለዩክሬን ከጦር መሳሪያ እስከ ሰብዓዊ ቁሳቁስ የሚደርስ ድጋፍ ሲልኩ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን ተጨማሪ ድጋፎችንም ለማድረግ አቅደዋል፡፡ ሀገራቱ በዩክሬን ጦርነት መሳተፍ አደጋ እንዳለው በመግለጽ ላይ የነበሩ ቢሆንም አሜሪካ ግን በተለያዩ የዘመቻ ተልዕኮዎች ላይ እንደተሳተፈች እየተገለጸ ነው፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ከገቡ ከሶስት ወራት በላይ የተቆጠሩ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ የሩሲያ ጦር ተጨማሪ የዩክሬን ግዛቶችን መቆጣጠሩን አስታውቋል፡፡
የሩሲያ ጦር ተጨማሪ የዩክሬን ግዛቶችን መቆጣጠሩን ቢገልጽም በጉዳዩ ላይ ከዩክሬን ፕሬዝዳንትም ሆነ ከመከላከያ ሃይሉ የተሰጠ ምላሽ ወይም ማብራሪያ አልተሰማም፡፡