ፑቲን ስሎቫኪያ ከዩክሬን ጋር የሚደረግን የሰላም ንግግር ልታስተናግድ እንደምትችል ገለጹ
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ጦርነቱ እንዲቆም ስሎቫኪያ ያቀረበችውን የንግግር ሀሳብ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል
ስሎቫኪያ ዩክሬንን ለመደገፍ ጥርጣሬ ካደረባቸው እና ከሩሲያ ጋር የሚደረግን ድርድር ከሚደግፉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል አንዷ ነች
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ጦርነቱ እንዲቆም ስሎቫኪያ ያቀረበችውን የንግግር ሀሳብ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።
ፑቲን አክለውም ሩሲያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ቁርጠኛ ነች ብለዋል።
የስሎቫኪያ ባለስልጣናት "... ሀገራቸው የድርድር መድረክ ብትሆን ደስተኛ ናቸው። ያ የሚሆን ከሆነ እኛ አንቃወምም። ስሎቫኪያ ገለልተኛ አቋም እስከያዘች ድረስ፣ ለምን አይሆንም" ሲሉ ተናግረዋል ፑቲን።
ስሎቫኪያ ዩክሬንን ለመደገፍ ጥርጣሬ ካደረባቸው እና ከሩሲያ ጋር የሚደረግን ድርድር ከሚደግፉ የማዕከላዊ እና የምስራቅ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል አንዷ ነች።
የስሎቫኪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁራጅ ብላናር ስሎቫኪያ ጦርነቱ በሰላማዊ መፍትሄ እንዲቋጭ ለረጅም ጊዜ ስትፈልግ መቆየቷን እና የፑቲን አስተያየት "አዎንታዊ ምልክት" መሆኑን ተናግረዋል።
ብላነር ትናንት ባወጡት መግለጫ "የስሎቫኪያ ዲፕሎማሲ ለሰላማዊ መፍትሄ አስተዋጽኦ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፤ ይህን አማራጭ ለዩክሬን አቅርበናል" ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከዩክሬን የምትዋሰነው ስሎቫኪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ በ2023 በድጋሚ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለሩሲያ አውንታዊ እይታ አላቸው ሲሉ በተደጋጋሚ እየተቿቸው ነው።
ፑቲን ከዩክሬን ጋር ያለው ጦርነት እንዲቆም ንግግር ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ነገርግን ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን ያቀደችውን ሳታሳካ ማጥቃቷን እንደማታቆም ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ፑቲን በትናንትናው እለት ሩሲያ ኦሬሽኒክ የተባለውን አዲስ የመካከለኛ ርቀት ሚሳይል ልትጠቀም እንደምትችል፣ ነገርግን ይህን ለማድረግ እንደማትቸኩል ተናግረዋል።
"አስፈላጊ ከሆነ ዛሬም ሆነ ነገ ከመጠቀም ወደኋላ የምንልበት ሁኔታ አይኖርም" ብለዋል ፑቲን።
ፑቲን እንደገለጹት አስፈላጊ ከሆነ ሩሲያ ኃይለኛ የሆኑ ተጨማሪ የመካከለኛ ርቀት ሚሳይሎችን ልትጠቀም ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።